Äthiopisch Orthodoxe Tewahedo Debre Bistrat St. Gabriel Kirchengemeinde München e.V.

በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሀዶ ቤተክርስትያን፣የሙኒክ ደብረ  ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን 

                                መዝሙር

መዝሙር ዘመረ ካለው ከግዕዙ አንቀጽ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም አመሰገነ  ማለት ነው። ይኽውም ከዓለማዊ ዘፈን ጋር የማይገናኝ ልዩ ልዩ ስልትና ቃና ባለው ድምጽ የሚዜም በዜማ ዕቃ የሚቀርብ መንፈሳዊ ምስጋና ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መለዕክቱ እንደጻፈው በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ ኤፌ 5፣19። ከዚህ ሌላ ቅዱስ ያዕቆብ "ደስ የሚለዉ ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር " በማለት ጽፏል (ያዕ 5፥13)። ስለዚህ ለክርስቲያን መዝሙር የዘወትር ተግባሩ ሊሆን ይገባል።

  

 


 

 

 





በክርስቲያን ሥርዐተ አምልኮ ዉስጥ መዝሙር ከፍተኛ ቦታ አለዉ። እስራኤላውያን ከጥንት ጀምሮ በተለይም ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ከጸሎትና መጽሐፍን ከማንበብ ጋር መዝሙር በመዘመር እግዚአብሔን ያመልኩ ነበር። |<አናጢዎቹም የእግዚአብሔርን መቅደስ በመሠረቱ ጊዜ ካህናቱ ልብሳቸውን ለብሰው መለከቱን ይዘው፥ የአሳፍም ልጆች ሌዋውያን ጸናጽል ይዘው እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት ሥርዓት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ>ዕዝ3፣10ክርስትናም ከስብከቱ፣ ከጸሎቱ፣ ከስግደቱ . . . ጋር አብዛኛዉ የአምልኮታችን ክፍል መዝሙር ነውመዝሙር ምስጋና እንደመሆኑ መጠን በግልና በኅብረት ከጸሎት ጋር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት ነው (ቆላ 4፥2)። በብሉይ ኪዳን  መስዋዕት በምኒቀርብት ጌዜእንስሳት፣ መሰዋዕት በተለያየ ምክንያት ለእግዚአብሔር ይሰዋ ነበር። ነገር ግን ከዚህ ይልቅ እግዚአብሔር ንጹሕና የዋህ በሆነ ልብ የሚቀርብ የከንፈራችንን ፍሬ እርሱም የምስጋና መስዋዕትን እንድናቀርብለት በቃሉ ነግሮናል (መዝ 49፥14፣ ዕብ 13፥15፣ ሆሴዕ 14፥2)። በአንዳንድ ዘማርያን እንደሚታየው የሥጋዊ ፍላጎት መፈጸሚያ ፣መተዋወቂያ በማድረግ ከመንፈሳዊ ስሜት ውጭ ይዘምሩታል። ይህም የዜማሪውን በሌላ ሥራና ሐሳብ መጠለፉንና መዝሙርን ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ እየተጥቀመበት መሆኑን ያሳያል  ። እግዚአብሔር ግን ከመዘመራችን በፊት የእኛ ሰውነት ሕያው ቅዱስም መስዋዕት ሆኖ እንዲቀርብለት ይፈልጋል (ሮሜ8፥12)። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሰዋዕቱ ተመለከተ ይለናል እንጂ ቀጥታ ወደ መስዋዕቱ ተመለከተ አይለንም (ዘፍ 4፥4)። እኛ መንፈዊውን በረከትና ጸጋ እያሰብን ሳሆን በተቃራኒው ሥጋዊና ጊዜያዊ ፍላጎት እያሰብን ብንዘምር እንዲሁ የከንፈር ድካም ብቻ ስለሚሆን እንደ ቃየል መሰዋዕት ተቀባይነት አይኖረዉም።









ቅድመ ዓለም በባሕርዩ ምስጉን የነበረ ዛሬም በጥረቱ የሚመሰገን እግዚአብሔር ሌሎችን ፍጥረታት  ለአንክሮ ለተዘክሮ ሲፈጥር ሰውንና መላእክትን ግን የፈጠረው በተሰጣቸው ዕውቀት ተጠቅመው ክብሩን እንዲወርሱና ስሙን እንዲቀድሱ ነው። ቅዱሳን መላእክት ሱራፌልና ኪሩቤል ክፋንፋቸውን ዘርግተው ያለዕረፍት " ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር " በማለት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ እየዘመሩ እግዚአብሔርን እንደሚያመሰኑት ተዘግቧል (ኢሳ 6፥1-5፣ ራዕይ 4፥8-11፣ መዝ 102፥20)። ሰማያውያን መላእክት እንዳመሰገኑት ሁሉ ምድራዊያን ሰዎችም ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን ማቅረብ ይገባናል። " ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑት"ይላል (መዝ 95፥1-2)። በእርግጥ ሌሎችም ፍጡራን በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ ተብለዋል (መዝ 148፥1-13)። ሆኖም ከሰውና ከመላእክት በስተቀር የእግዚአብሔርን ክብር የመውረስ ዕድል ስለሌላቸው ምስጋናቸው ጊዜያዊ ነው። ሰውና መላእክት ግን የተፈጠሩት እግዚአብሔርን በማመስገን እንዲኖሩ ነው። ስለዚህ እኛም እንደ ቅዱስ ዳዊት " በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ" (መዝ 145፥2)። በማለት ልናመሰግን ምስጋናም የዘወትር ሥራችን ሊሆን ይገባል።











መዝሙር በመጽሐፍ ቅዱስ

በመጽሐፍ ቅዱስ የመዝሙር ታሪክ ከጥንት ጀምሮ ከእምነት ታሪክ ጋር አብሮ ተተርኳል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዱ መጽሐፍ መጽሐፈ መዝሙር ነው። ይኸውም መዝሙረ ዳዊት የሚባለው ነው። መዝሙረ ዳዊት የተባለው መጽሐፍ በውስጡ ከያዛቸው 150 ያህል መዝሙሮች ውስጥ ( 82ቱ) በዘማሪነት የሚታቀው የቅዱስ ዳዊት መዝሙራት ስለሆኑ ነው እንጂ፤ በመጽሐፉ ውስጥ በሌሎች መዘምራን (ቆሬ፣ አሳፍ፣ ኤማንና፣ ሐጌ ዘካርያስ . . . ) ስም የተጠቀሱ መዝሙሮች ይዟል። በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ብዙ የእምነት ሰዎች በየምክንያቱ የዘመቻቸው መዝሙሮች ከታሪኩ ጋር ተመዝግበው ይገኛሉ። በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን በየዘመናቱና በየጊዜው የተፈጸመውን የመዝሙር ታሪክ እንደሚከተለው እናያለን።        

በብሉይ ኪዳን

ሀ) እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ የዘመሩት መዝሙር

እግዚአብሔር በበረታች ክንድ ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት በሙሴ አማካይነት እስራኤላውያንን ነጻ ካወጣቸው በኋላ ታላቁን የእግዚአብሔርን ማዳን አዩ። ይኸውም ሕዝቡን እስራኤልን ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ በየብስ ካሻገረ በኋላ የሚያስድዷቸውን ግብጻውያንን ፈርኦንና ሠራዊቱን ፈረሱንና ፈረሰኞችን እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ ጣላቸው። ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ በእግዚአብሔርም በባሪያውም በሙሴ አመኑ (ዘጸ14፥26-31)። በዚያን ጊዜም ባሕሩን ከተሻገሩ በኋላ ሙሴና የእስራኤል ልጆች " በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ" በማለት ረጅም መዝሙር ዘምረዋል። የሙሴና የአሮን እህት ነብይቱ ማርያም ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ይህንኑ መዝሙር በከበሮ እየዘመረች መልሳዋለች (ዘጸ 15፥1-21)።



















እስራኤል ቀይ ባሕርን ሲሻገሩ።

ሙሴ የሕዝብ መሪ ሆኖ ሳለ ከሕዝብ ጋር እግዚአብሔርን አመሰገነ። ዛሬም ቢሆን ታላላቆችም ታናናሾችም እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑት ይገባቸዋል ( ራዕይ 19፥5)። የአገር ሽማግሌ፣ አገረ ገዢ፣ የሕዝብ መሪ መሆን ከመዝሙር ሊለይ አይችልም። ማርያምና ሌሎችም ሴቶች በክብር መዝሙሩን መዘመራቸው ምስጋና በጾታም የማይገደብ መሆኑን ያሳያል። ሴቶችም ቢሆኑ በሕዝብ ጉባኤ በአደባባይ በከበሮ፣ በሽብሸባ፣ በጭብጨባና በእልልታ እያደመቁ ያለፍርሃት መዘመር ይገባቸዋል (መዝ 67፥25)።











እስራኤላውያን የዘመሩት መዝሙር ባሕሩን ከፍሎ ባሻገራቸው ጊዜ ያሳየውን የማዳን ኃይል እያወሳ እግዚአብሔርን የሚያመሰግን ነው። ዛሬም ቢሆን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የኃጢአትና የሞት ባሕር ተከፍሎ ዲያብሎስም ወደ ጥልቅ የእሳት ባሕር የተሻገረበትና እኛ የዳንበት ጊዜ ነው። ከዚህም በላይ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ የችግሮን፣ የኑሮ ፈተናን ባሕር እየከፈለ በድል ያሻግረናል። እኛም እግዚአብሔርን ካመለክነው ከፍ ከፍ ካደረግንና ካከበርነው በኋላ ባደረገልን ነገር ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል።

ለ) እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው የምስክር መዝሙር

ይች መዝሙር ሙሴ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆች ላይ ወደፊት ምስክር እንድትሆን የተሰጠች መዝሙር ነች። ከሙሴ በኋላ ሕዝቡን በመሪነት የሚረከበው ኢያሱ ከሙሴ ጋር በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አብረው እንዲቆሙ ከተደረገ በኋላ ወደፊት ሕዝቡ ሌሎች አማልክትን ሲከተል ምስክር ትሆን ዘንድ ይችን መዝሙር እንዲጽፍና ለሕዝቡ እንዲያስተምሩ ተደረገ (ዘጸ 3፥14-30)። ይች መዝሙር " ሰማያት ሆይ! አድምጡ እኔም እናገራለሁ ምድርም የአፌን ቃል ትስማ " ብላ በመጀመር (ዘጸ 30፥19, ዘዳ 32፥1, ኢሳ 1፥2)። ሰማይና ምድር ታስመሰክራለች። ይችህ መዝሙር የምስክር መዝሙር ብቻ ሳትሆን የትምህርትና የመታሰቢያ መዝሙር ናት። ሌሎች አማልክት ሲከተሉ ከዚህች መዝሙር ትምህርት አግኝተው እንዲመለሱና የቀደሙትን እውነተኛ የእምነት አባቶቻቸውንና መሪዎቻቸዉን እንዲያስታውሱ እንዲያስቡ ታደርጋቸዋለች።









"ንሴብሆ ለእግዚአብሔር!" በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን

በድምቀት ሲዘመር።

መዝሙር እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ግጥምና ዜማ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ለሕዝቡ በከንፈሩ የሚተዉለት መልዕክትና ትምህርት መሆኑን ከዚህ እንረዳለን። ስለዚህ ዛሬም ቢሆን በተለያየ ምክንያት አገር በመቀየር፣ በሞት . . . አገልግሎታችንን የምናጠናቅቅ ከሆነ በሕዝቡ የሚቀር መታሰቢያና ትምህርት እንዲሁም ምስክር የሚሆን መልዕክት ያለው መዝሙር ማስተማር ይገባናል። ሕዝበ ክርስቲያኑንም ቢሆን ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ አባቶች የተጻፉለትን መልዕክት አዘል መዝሙሮች እያስተዋለ ተምሮ በማጥናት ሊመከርበት ሊገሰጽበትና ሊለወጥበት ይገባል።

ሐ) በዘመነ መሳፍንት ነቢይት ዲቦራና ባርቅ የዘመሩት መዝሙር (መ. መሳ 5)

መዝሙር በዘመነ መሳፍንትም እግዚአብሔር የሚከበርበትና የሚመሰገንበት መንገድ ነበር። ነቢይት ዲቦራና ባርቅ በዘመነ መሳፍንት ለአራተኛ ጊዜ በእስራኤል መስፍን የነበሩ ናቸው። እንደሚታወቀው በዘመነ መሳፍንት በእስራኤል የነበረዉ መንግስት፤ መንግሥተ እግዚአብሔር ስለነበር እግዚአብሔር ሕዝቡን በቅርብ የሚረዳበት ዘመን ነበር። ሕዝቡም ስለሚደረግላቸው ነገር ያመሰግኑታል። በነቢይት ዲቦራና ባርቅ ዘመን በአሶር የነገሰው የከነዓን ንጉሥ ኢያቢስ ከሃያ ዓመት በላይ እስራኤልን ባስጨነቀ ጊዜ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። ነቢይት ዲቦራ ባርቅን አስነስታ ከአሥር ሺህ ሰዎች ጋር ወደ ታቦር ተራራ አብራዉ ወጣች። የኢያቢስ ሠራዊት አለቃ ሲሳራ ከነሠራዊቱ በተንቀሳቀሰ ጊዜ እግዚአብሔር በባርቅ ፊት ወጣ። ሲሳርና ሠራዊቱ ድል ተመቱ (መ. መሳ 4፥1-24)።

ከዚህ በኋላ ዲቦራና ባርቅ ለእግዚአብሔር ክብር እየተቀኙ ዘምረዋል። . . . . . . . . . . . . ሲዘምሩም "እኔስ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ ለእስራኤል አምላክ እዘምራለሁ " (መ. መሳ 5፥3) በማለት ሲሆን የደረሰባቸውን መከራ በማስታወስ እንዲሁም ደግሞ ባገኙት ድል እግዚአብሔርን በማመስገን ነው።

ዛሬም ቢሆን በችግርና በጭንቅ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር መጮኽ ይገባናል። ጩኸታችንንም በመዝሙር ልንገልጽ እንችላለን (መዝ 119፥1) እግዚአብሔርም ይሰማናል ይደርስልንማል። ታዲያ በመከራና በጭንቀት ጊዜ የልቅሶ ቅኔ እየተቀኘን ያስታወስነውንና የለመነውን አምላክና አባት በድል ጊዜ በደስታ ልንዘነጋው አይገባም። በእግዚአብሔር ኃይል ባገኘነው ድል ራሳችንን ማመስገን የለብንም። በተለይ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የምናገለግል ሰዎች እግዚአብሔርን በሕዝቡ ውስጥ በድል ስናየው በመቀኘትና በመዘመር ልናመስግነው ይገባል። መዝሙራችንም ያለፈውንና የአሁኑን፣ መከራውንና ድሉን የሚያስታውስ ሊሆን ይገባዋል። እግዚአብሔር ለድልና በድል የተገለጠባቸውን ሰዎችን ስም በመዝሙራችን ውስጥ ማንሳት እንችላለን። ለምሳሌ በዚህ መዝሙር ውስጥ የዲቢራ፣ የባርቅ፣ የዛብሎንና የንፍታሌም ነገድ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል ተጠቅሰዋል (መ. መሳ 5፥1, 5፥18, 5፥24)። እንዲህም ከሆነ በተለይም በአዲስ ኪዳን በሰይጣን ላይ ለተገኘው ድል እግዚአብሔር መሳሪያ ያደረጋቸውን ቅዱሳን በመዝሙራችን ማንሳት ያስፈልጋል። ደግሞ በግልና በማኅበር በደረሰብን መከራና ጭንቀት እግዚአብሔር ድል ሲሰጠን በመሳሪያነት የተገለጠባቸውን እያወሱ መዘመር ምስጋናችንን በበለጠ ያከብረዋል ያደምቀዋልም።

መ) መዝሙር በዘመነ ነገሥት

በእስራኤላዊያን ዘንድ መዝሙር በተደራጀ ሁኔታ በመዘምራንና በዜማ ዕቃዎች በዕለተ ሰንበትና በተለያዩ በዓላት ይዘምር የነበረው በዘመነ ነገሥታት እንደሆነ መጻሕፍተ ነገሥትን ስናነብ እንረዳለን። ከመደበኛው የመዝሙር አገልግሎት ውጪም በተለያዩ ምክንያቶች ለእግዚአብሔር ክብር ይዘመር ነበር። አሁን በመጠኑ የምንመለከተው በሚከተሉት አራት ነገሥታት ዘመን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸልንን የመዝሙር ታሪክ ይሆናል።

1. በዳዊት    2. በሰሎሞን  3. በኢዩሳፍጥ  4.በሕዝቅያስ

1) መዝሙር በዳዊት ዘመን

ቅዱስ ዳዊት የሚታወቀው በንጉሥነቱ ብቻ ሳይሆን በዘማሪነቱም ጭምር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው የመዝሙር መጽሐፍ በስሙ ተሰይሟል። ከመዝሙሮቹ ውስጥ በሰማንያ ሁለቱ ላይ የእርሱ ስም ተጠቅሷል። ልበ አምላክ የተባለው ቅዱስ ዳዊት በገና በመደርደር መዝሙር የጀመረው ከንጉሥነቱ በፊት ነው። ወደ ሳኦል ቤተ መንግስት እንዲገባ መሰረታዊ ምክንያት የሆነው የኸው በገና የመደርደር ችሎታው ነበር። በሳሙኤል እጅ ለንጉሥነት ከተቀባ በኋላ በዳዊት ላይ መንፈሰ እግዚአብሔር ሲያድርበት በሳኦል ላይ ግን ክፉ መንፈስ አደረበት። ስለዚህ ክፉ መንፈስ እንዲርቅለት ባሪያዎቹ ባቀረቡለት ሐሳብ መሰረት ሳኦል ዳዊትን አስመጥቶ በገና እንዲደረድርለት አደረገ። ክፉው መንፈስም ከሳኦል እንዲርቅለት አደረገ። ክፉው መንፈስም ከሳኦል ራቀ ዳዊትም በሳኦል ፊት ሞገስን ስላገኘ ጋሻ ጃግሬው ሆነ (1ኛ ሳሙ 16፥14-23)። ነገር ግን ሳኦል እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደሆነ ሲያውቅ ፈራውና ብዙ ጊዜ ሊገድለው ፈለገ። እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ለዳዊት ጠላት ሆኖ ቀረ። እግዚአብሔር ግን ዳዊትን ከሳኦልና ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ አዳነዉ። ይህን በተመለከተ ዳዊት (በ2ኛ ሳሙ 22፥1-51) ያለውን መዝሙር ዘምሯል

ዳዊት በእስራኤል ላይ ከነገሠ በኋላ በኤሊ ዘመን መጨረሻ ላይ የተማረከውን የእግዚአብሔር ታቦት ከአሚናዳብ ቤት ተመልሶ እንዲመጣ ባደረገ ጊዜ ከእስራኤል ቤት ጋር በሙሉ ኃይሉ ይዘምር ነበር። ይህንንም ሲገልጽ "ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመስንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጽናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር " ይላል (2ኛ ሳሙ 6፥5)። ከዚያም በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ከተቀመጠ በኋላ ታቦቱ ወደ ዳዊት ከተማ ሲመጣ በብዙ ክብር ነበር። ዳዊትም በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይዘፍን ነበር። የእስራኤል ቤትም ሆ! እያሉ ቀንደ መለከት እየነፉ እግዚአብሔርን አክብረዋል። የሳኦል ልጅ ሜልኮን ግን ዳዊትን በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይሉ ሲዘልና ሲዘፍን ባየችው ጊዜ በልብዋ ናቀችው በቃልዋም ተናገረችው። እርሱ ግን "በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ" ብሎ ሳያፍር ተናገራት። እርሷም እስከ ሞተች ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም (2ኛ ሳሙ 6፥16-23)።

ቅዱስ ዳዊት በተከለው ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉ ሦስት መዘምራን አደራጅቷል። የአለቆችም ስም ኤማን፣ አሳፍ እና ኤዶታም ነበር። ለነዚህም ክናንያ የሚባል የመዝሙር (የዜማ) አስተማሪ ነበራቸው። አገልግሎታቸውም በተራ በሰሎሞን ነበር። ዳዊት በአጠቃላይ 288 መዘምራን ነበሩት። ዳዊትም በአደባባይ ሳይውል ከእነርሱ ጋር እየተገኘ ይዘምር ነበር (1ኛ ዜና 15፥16-24, 1ኛ ዜና 25፥1-10)።

ዛሬም ቢሆን እንደ ቅዱስ ዳዊት ሁለገብ የሆነ የመዝሙር ሰው መሆን ይገባል። ቅዱስ ዳዊት በገና ይደረድር ነበር፤ እየተቀኘም ይዘምር ነበር። ከዚህም የምንረዳው ከመዝሙር ጋር የዜማ መሳሪያዎችን የመምታት ችሎታ ሊኖረን ያስፈልጋል። በየጊዜውም በመቀኘትና በመዘመር እግዚአብሔርን እንድናመሰግን ለሌሎችም ሰዎች እንድንተርፍ ይገባል። የእግዚአብሔር ቃል " ተቀኙለት ዘምሩለት" ይላል (1ኛ ዜና 16፥9)። በዚህም እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ብቻ ይሆን ዘንድ ይገባል። ያም ከሆነ ለአመስጋኙ እንደ ሳኦል የክፋት መንፈስ እንዳያድርበት ክፉ መንፈስን ያርቅለታል።

ዳዊት ከንጉሥነቱ በፊት ብቻ ሳይሆን በሹመቱና በንጉሥነቱም እያለ ለእግዚአብሔር ዘምሯል። በግሉ ብቻ ሳይሆን ከመዘምራኑ ጋር በቤቱም ብቻ ሳይሆን በአደባባዩ እግዚአብሔርን በመዝሙር አክብሯል። እኛም በሕጻንነታችን ለእግዚአብሔር የመዘመር ፍቅር የነበረንን ያህል በእድሜ ከፍ ብንልም ሥራ ብንይዝም ትዳር ብንመሰርትም ሹመትና ሥልጣን ብናገኝም የዚህ ሁሉ ባለቤት የሆነውንና ለዚህ ያበቃንን ልዑል አምላክ በግልና በሕዝብ ፊት ልናመስግነውና በሙሉ ኃይላችን ልናሸበሽብለት ይገባል። በዳር ሆኖ የሚዘምሩትን መናቅ እና መተቸት ግን እንደ ሜልኮን መሆን ነው። እግዚአብሔር የሚንቁትን ይንቃቸዋል ፤ የሚስቁትን ይስቅባቸዋል ደግሞም ይቀጣቸዋል። ስለዚህ በተለይም ዛሬ በቤተክርስቲያን ስሙ የተጻፈበት ጽላት ወጥቶ እግዚአብሔር በሚከብርበት በዓለ ንግሥ ላይ እግዚአብሔርን ከማመስገን ጋር ሳናፍር እምነታችንን ልንመሰክር ያስፈልጋል።












ንጉሥ ዳዊት በገና እየደረደረ ፈጣሪውን ሲያመሰግን።

ከዚህም ሌላ የበዓል ቀን ዘማሪዎች ብቻ ልንሆን አይገባም። ያ ከሆነ ለተርዕዮ (ለታይታ) ብቻ ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ ቅዱስ ዳዊት እንዳደራጃቸው መዘምራን በሁለት፣ በሦስት ቡድን ከዚያም በላይ ተደራጅተን በሰንበት ትምህርት ቤትና በቤተክርስቲያን በየሳምንቱ በየተራ ቋሚ የመዝሙር አገልግሎት ልንሰጥ ያስፈልጋል።

2) መዝሙር በሰሎሞን ዘመን

ከዳዊት ጀምሮ በተደራጁ መዘምራን የተጀመረው የመዝሙር አገልግሎት እንደቀጠለ ነው። በሰሎሞን ዘመን በበለጠና በተሻሻለ ሁኔታ ይዘመር ነበር። አሁን በዚህ ርዕስ የምናየው ግን ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሰርቶ በጨረሰ ጊዜ እንዴት እንደተዘመረ ይሆናል ።

የቤተ መቅደሱ ሥራ እንደተጨረሰ የእግዚአብሔር ታቦት በካህናት አማካይነት ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ እንዲገባ ተደረገ። በዚህ ጊዜ በሰሎሞን ሳይከፈሉ ሦስቱንም ቡድን መዘምራን ጥሩ በፍታ ለብሰዉ በጸናጽል በበገና በመሰንቆ በዜማ ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። የሚዘምሩትም "እግዚአብሔር ቸር ነዉና ምህረቱም ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ" የሚል መዝሙር ነበር። ለድምቀቱም ካህናት መለከት ይነፋ ነበር። የእግዚአብሔርም ክብር በደመና ተገልጦ ቤቱን ሞላው (1ኛ ዜና 5፥11-14)።

 

ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ረዘም ያለ ጸሎት አድርጎ የሚቃጠል መስዋዕት ቀረበና ሕዝቡና ካህናቱ ንጉሡም እግዚአብሔርን በመዝሙር አመሰገኑ። ሌዋውያን የዘመሩትም "ምህረቱም ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑት" የሚለውን የዳዊት መዝሙር ሲሆን የዘመሩትም ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔርን ለማመስገን የሠራውን የእግዚአብሔርን የዜማ ዕቃ በመጠቀም ነበር (2ኛ ዜና7፥4-7)።

ዛሬም ቢሆን ለእግዚአብሔር ታቦት ማደሪያነት ትሆን ዘንድ ቅድስት ቤተክርስቲያን ስትከብርም ሆነ ማንኛውም በዓል ሲከበር ሁሉም መዘምራን ዩኒፎርም ለብሰው መዘመር ይገባቸዋል እንጂ፤ እንደ ዘወትር አገልግሎት ተራ (ሰሞን) መጠበቅ አያስፈልጋቸውም። ሕዝቡም ከመዘምራኑ ጋር በተለያዩ የዜማ ዕቃዎች እያደመቀ እግዚአብሔርን ማመስገን አለበት።


















3) መዝሙር በኢዮሳፍጥ ዘመን

በአራተኛው የይሁዳ ንጉሥ በኢዮሳፍጥ ዘመን እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በመዝሙራቸው ተገልጦ ጠላቶቻቸውን እንዳሸነፈላቸው ተመዝግቧል። የሞዓብና የአሞን ልጆች ከእነርሱም ጋር ሞአባውያን ኢዮሳፍጥን ሊወጉ በመጡ ጊዜ ኢዮሳፍጥ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ የእግዚአብሔርን ኃይል በጾምና በጸሎት ጠየቀ። እግዚአብሔርም መንፈሱን በሕዝቅኤል ላይ ገልጾ ሰልፉ የእግዚአብሔር ስለሆነ እነርሱም ዝም ብለው በመቆም የእግዚአብሔርን ማዳን እንዲያዩ እንዳይፈሩና እንዳይደነግጡ ተናገራቸውም። ማልደውም በመነሳት ከሕዝቡና ከሠራዊቱ ፊት መዘምራንን በእምነት አቆሙ። መዘምራኑም ጌጠኛ ልብስ ለብሰው ነበር። እነርሱም "ምህረቱም ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑት" የሚለውን መዝሙር ገና ሲጀምሩ እግዚአብሔር ሊወጉዋቸው በመጡት ላይ ድብቅ ጦርን አመጣባቸው እነርሱም ተመቱ። ከዚህ ድል በኋላ ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች በፊታቸውም ኢዮሳፍጥ ደስ እያላቸው በበገና በመስንቆ በመለከትም ወደ እግዚአብሔር ቤት ገቡ (2ኛ ዜና 20፥1-30)።

ዛሬ ግን ምድራዊ የሆነ የእግዚአብሔር ሰልፍ አናይም። ብዙዎች ሰልፈኞች በሽለላ በፉከራ በዘፈን የሚገልጹት የራሳቸውን ኃይል እንጂ የእግዚአብሔርን ኃይል አይደለም። ክርስቲያኖች ግን ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጸልን ከሰይጣንና ከሠራዊቱ ጋር በምናደርገው ሰማያዊ ሰልፍ (ጦርነት) ውስጥ በራሳችን ጥበብና ኃይል ሳይሆን በመዝሙራችን የእግዚአብሔርን ኃይል በመግለጥ ልንዋጋውና ልናሸንፈው እንችላለን። ከድል በኋላም ደስ ብሎን እየዘመርን በቤቱ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል። መዝሙራችን ጌጠኛ ልብስ በለበሱ መዘምራን ሊመራ እንደሚገባ ከዚህ ታሪክ እንረዳለን።

4) መዝሙር በሕዝቅያስ ዘመን

ሕዝቅኤል በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ካህናቱንና ሌዋዉያንን ሰብስቦ የእግዚአብሔር ቤት እንዲታደስ አደረገ። ካህናቱንና ሌዋዉያኑን የእግዚአብሔርን ቤት ካነጹትና ከቀደሱት በኋላ ሕዝቅያስ የተለያዩ ዓይነት መስዋዕት እንዲቀርብ አደረገ። ይህ መስዋት ሲቀርብ መዝሙር እየተዘመረ ነበር። ሕዝቅያስ ጽናጽልና በገና መሰንቆም አስይዞ መዘምራን አቆመ መስዋዕቱም ማረግ በጀመረ ጊዜ በእነዚህ የዜማ መሳሪያዎች ታጅቦ የእግዚአብሔር መዝሙር ተጀመረ። ሕዝቡ እየሰገደ መለከት እየነፋ በመዘመር መሰዋቱን አቅርበው ሲጨርሱ ንጉሡ ሕዝቅያስና አለቆች በዳዊትና በአሳፍ መዝሙሮች እግዚአብሔር እንዲመሰገን አደረጉ ሁሉም በደስታ አመሰገኑ።

እኛም ዛሬ በሰእለታችን፣ በስግደታችን፣ በምጽዋታችን፣ በጾማችን፣ በልግስናችን . . . የምናቀርበው መስዋዕት ሁሉ እግዚአብሔርን በዝማሬ እያመሰገንን ልናቀርብ ያስፈልጋል። ሰዎች ራሳቸውን ከቀደሱና ካቀረቡ በኋላ የእግዚአብሔር መሆናቸውን የሚገልጹ ለስሙ በመዘመራቸው ነው። ከዚህ ታሪክ እንዳየነው የቤተ መቅደስ መታደስ የሰዎችን መታደስ ያሳያል ከዚያ በፊት ያረከሱት ሰዎች ነበሩና። ይህንንም የገለጡት በመዝሙርና በመሰዋዕት ነው። የዘመሩትም ቀድሞ በዳዊት ዘመን በተዘመረባቸው የዜማ መሳሪያዎችና መዝሙሮች ነው። ዛሬም ቢሆን በዳዊት ዘመን የነበረውን ሥርዓተ መዝሙር ልንከተል ይገባል። እንደቀድሞ አባቶች በገና በመደርደር ጽናጽልና መሰንቆ በመምታት መለከት በመንፋት የተዘነጋውን የዳዊትን መዝሙር ልናዳብር ይገባል።










ሠ) መዝሙር ከባቢሎን ምርኮ መልስ

እስራኤላዊያን በባቢሎን ምርኮ በነበሩ ጊዜ በባዕድ ምድር በምርኮ አገር መዝሙራቸውን እንዳልዘመሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል (መዝ 136፥1-5)። ከባቢሎን ምርኮ መልስ ግን ሁለት መቶ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ነበሩ (ዕዝራ 2፥65)። በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ትእዛዝና ፈቃድ መሰረት ፈርሶ በነበረው በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ምትክ በዚያው ቦታ አዲስ ቤተ መቅደስ ለመስራት አናጢዎች መሰረት ሲጥሉ ካህናቱና ሌዋውያኑ በቀድሞው በንጉሥ ዳዊት ሥርዓት መሰረት ልብስ ለብሰው ጸናጽል ይዘው መለከት እየነፉ እግዚአብሔርን አመሰገኑት። የሚዘምሩትም "ቸር ነውና ለእስራኤልም ምህረቱ ለዘላለም ነውና" የሚለውን በማስተዛዘል ነበር። ሕዝቡም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ደስ ብሏቸው በታላቅ ድምጽ እልል ይሉ ነበር። በአንጻሩም ደግሞ የፊተኛውን ቤት ያዩ ሽማግሌዎች በትዝታ ተወስደው በታላቅ ድምጽ ያለቅሱ ነበር። በዚህም የእልልታውንና የለቅሶውን ጩኸት ለመለየት እስከሚያስቸግር ድረስ በታላቅ ፍቅር ይዘመር ነበር (ዕብራ 3፥1-13)። አንዳንድ ፈተናዎችን አልፎ የቤተ መቅደሱ ሥራ በተጠናቀቀ ጊዜ ደግሞ ቅዳሴ ቤቱን በታላቅ ደስታ አክብረዋል (ዕዝራ 6፥13-18)። ከሌሎች የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ጋር መዘምራንም ከግብርና ከቀረጥ ነጻ ሆነው እንደ ቀድሞው ሥርዓት እግዚአብሔርን ያገለግሉ ነበር (ዕዝራ 24)፣ ነህምያ 11፥22-24)።











በሌላ በኩል ደግሞ በነህምያ መሪነት የኢየሩሳሌም ቅጥር ከተሰራ በኋላ ሌዋውያኑና መዘምራኑ ከሰፈሩት ቦታ ተፈልገው መጥተው የምረቃውን (የቅዳሴውን) በዓል በደስታና በምስጋና በመዝሙር አክብረዋል። አጥሩ ከመሰራቱ በፊት መዘምራኑ በኢየሩሳሌም መንደሮች ሰርተው ነበር። ከዚያም ተሰብስበው ራሳቸውን ካጸኑ በኋላ አመስጋኞች በሁለት ተርታ ተከፈሉ። እንደ ጸሐፊው በዕዝራ መሪነት አንዱም በነህምያ መሪነት ቅጥሩን እየዞሩ በእግዚአብሔር ሰው በዳዊት የዜማ ዕቃ በታላቅ ድምጽ ዘመሩ በዚህን ጊዜ የመዘምራን አለቃ ይዝረህያ ይባል ነበረ ( ነህምያ 12፥27-43)።

ከባቢሎን ምርኮ በኋላ በአጠቃላይ የመዘምራን ሁኔታ እንደቀድሞው ሥርዓት ቀጥሏል። መዘምራኑም የዳዊትንና የሰሎሞንን ትዕዛዝ ጠብቀዋል። ልክ እንደ ዳዊት እንደ አሳፍ ዘመንም የመዘምራን አለቆች ነበሩ። መዘምራኑም በዘሩባቤልና በነህምያ ዘመን እንደ ሌሎች አገልጋዮች ሁሉ በየዕለቱ የሚገባቸውን ዕድል ፈንታ ከእስራኤላዊያን ያገኙ ነበር (ነህምያ 12፥44-47)። በዚያ ዘመን ከነበሩት ነብያት የሐጌና የዘካርያስ መዝሙሮች በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ተጠቅሰው ይገኛሉ (መዝ 145፥146-148)።

ከዚህም ታሪክ ብዙ ነገሮችን እንገነዘባለን በባዕድ ቦታ እንደ አሕዛብ የሆኑ ዓለማውያን ሰዎች ሊያሾፉበት ሊዝናኑበት እንድንዘምርላቸው ቢጠብቁን መታዘዝ የለብንም። መዝሙር ምስጋና እንጂ መዝናኛና መታወቂያም መሆን አይደለምና። በቤተክርስቲያን ስለምናደርገው የመዝሙር አገልግሎት ግን ያለጾታ ገደብ መዘምራን በመሆን መዘመር እንችላለን። ፈርሶ የነበረ የሰው ልጆች ሕይወት፤ ፈርሶ የነበረ ጉባኤ፤ ፈርሶ የነበረ ሥርዓት እንደ ቀድሞው ሲመለስ ልክ እንደ እስራኤል ወንዱም ሴቱም ልጆችም በአንድ ድምጽ ልንዘምር ይገባል። ስንዘምርም ፍቅራችን የሚገለጸው በደስታ እልል በማለት ብቻ ሳይሆን በታላቅ ልቅሶም ሊሆን ይችላል። ከዚህም አንዳንድ መዝሙሮችን በማስተዛዘል (በመቀባበል) መዘመር መዝመሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን እንረዳለን።

በሕዝብ ውስጥ ታላቅ ቦታ የነበራቸው ከመዘምራን ዕዝራ፤ ከባለስልጣን ነህምያ፤ ከነቢያት ሐጌና ዘካርያስ አብረው ዘምረዋል። ዛሬም እንዲሁ ሊሆን ይገባል። በተለይም በወንጌል ሥራ ውስጥ መዝሙር ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል ልክ እንደ ነህምያ ዘመን በንጽሕና ለሚያገለግሉ መዘምራን ሊታሰብላቸው ሊጸለይላቸው ይገባል። በእግዚአብሔር ፊት በታላቅ አገልግሎት የተሰየሙ ናቸውና።

                     2) በአዲስ ኪዳን

በጌታችን በሐዋርያት ዘመን የጌታ ተከታዮች ይዘምሩ እንደ ነበሩ በአዲስ ኪዳን ክፍል ተገልጧል። በብሉይ ኪዳን የተገለጸውም የቤተ መቅደስ የመዝሙር አዘማመር በአዲስ ኪዳን መንፈስ እየተመሰጠረ ሊቀጥል ይችላል። በአዲስ ኪዳን ክፍል የተመዘገበውን ያህል በሚከተሉት አርዕስቶች የመዝሙርን ታሪክ እናያለን።

1) የሆሳዕና መዝሙር      2) የምሴተ ሐሙስ መዝሙር            3) የወህኒ መዝሙር

4) የማህበር መዝሙር

 1) የሆሳዕና መዝሙር

ይህ መዝሙር የተዘመረው ጌታችን፣ መድኃኒታችን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ ሕይወት መጨረሻ አከባቢ ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት ጊዜ ነው። መዝሙሩም " ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ሆሳዕና በአርያም" የሚል መዝሙር ነው (ማቴ 21፥9)። መዝሙሩን የዘመሩት የጌታ ደቀ መዛሙርት (ተከታዮች) ናቸው (ሉቃ 19፥36)። በተለይም ሕጻናት በዚህ ቀን በይበልጥ ዘምረዋል (ማቴ 21፥15)። የሚዘምሩትም ጌታ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ከተማ ሲገባና ቤተ መቅደሱን ሲዞር ብዙ ሆነው በማጀብ፤ በፊትና በኋላ ሆነው የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ልብሳቸውን እያነጠፉ በታላቅ ፍቅርና መገዛት ነበር (ማር 11፥6-10)። በዚያን ጊዜ ደስ ብሏቸው በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ የቻሉት ተአምራትን ሁሉ ስላዩ ነው (ሉቃ 19፥37)። ፈሪሳውያን ምስጋናውን ቢቃወሙም ጌታ አልተቀበላቸውም።



















ሆሳእና።

የእግዚአብሔርን ቃል "እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ ለአሕዛብም ሥራዉን አውሩ ተቀኙለት ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ" ይላል (1ኛ ዜና 16፥8-9)። ዛሬም ቢሆን ዓለምን በድንቅ አሰራር የፈጠረውንና በፍቅር ያዳነውን እግዚአብሔርን ስለፍቅሩ፣ ስለማዳኑና ስለተአምራቱም ልናመሰግነው ይገባል። "ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው" የሚለውን መዝሙር አስቀድሞ በቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 117፥25 ላይ የተነገረ ነው። ዛሬም የሆሳዕና በዓል ሲከበር መዝሙር 117ን በሙሉ ቄሱ በከፍተኛ ድምጽ ሲናገር ሕዝቡ "በእግዚያብሔር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው።" እያሉ እየመለሱለት በዚህ ዓይነት እንዲባል የቤተክርስቲያን ሥራዓት ያዛል ( አንቀጽ 101)። በዚህ በዓል ልክ እንደዚያን ጊዜ ሰዎች ዘንባባ በመያዝ ታሪኩን የሚያስተውሱ ማዳኑን የሚገልጽ መዝሙር በስሙ የተሰየመውን (ካህን፣ ጽላት፣ መስቀል) አጅበን በብዙ ክብር ልንዘምር ይገባናል (ራዕይ 7፥9-10)።

እግዚአብሔር ለወደደው ይገለጣል። ተምረናል የሚሉት የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን እያሉ የሆሳዕናውን መዝሙር የገለጠው ላልተጠበቁ ሰዎች በተለይም ለሕፃናት ነበር። የካህናት አለቆች ጻፎችና ፈሪሳውያንም ሲያቅታቸው "እነዚህን የሚሉትን አትሰማምን? ደቀ መዛሙርትህን ገስጻቸው " በማለት ተመቀኙ። ጌታ ግን "ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ" የሚለውን የዳዊትን ቃል ጠቅሶ "እነዚህም ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮሃሉ" በማለት መልሶላቸዋል (ማቴ 21፥14-17፣ ሉቃ 19፥39-40፣ ዕዝ 8፥2)። እንደ ፈሪሳውያን እግዚአብሔር በሕፃናትና በምእመናን እንዳይመሰገን የሚቃወሙ ሰዎች ቢኖሩም እኛን ግን እንደ ድንጋይ ከምንሆነው ከእኛ ምስጋናን ያዘጋጃል። እኛም ማንኛውም ተቃውሞ ሳያግደን እንደ ሕፃናቱ በታላቅ በፍቅር ልንዘምርለት ያስፈልጋል።

2) የጸሎተ ሐሙስ መዝሙር

ይህ መዝሙር ጌታና ሐዋርያት የዘመሩት መዝሙር። ጌታችን በዚያ ምሽት እግራቸውን አጥቦ ሥጋውንና ደሙን ከሰጣቸው በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ከመውጣታቸው በፊት ዘምረውታል (ማቴ 26፥30)።

ያምሽት ጌታ ከሐዋርያት ጋር የሚቆይበት የመጨረሻው ምሽት ነበር ለማለት ይቻላል። ሆኖም የመዝሙሩ ቃል ምን እንደሆነ አልተገለጠም። ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ጌታ ለመከራና ለስቅላት የሚያዝበት ምሽት ስለሆነ ለሐዋርያት የሐዘን ምሽት ነበር። ሐዋርያት ከጌታ ጋር ይህን መዝሙር በምን ዓይነት የባባ ልቡና እንደዘመሩት ከዚህ መረዳት ይቻላል። በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሰረት "ዝማሬ" የሚባለው መዝሙር ለዚህ የምሴተ ሐሙስ መዝሙር መታሰቢያ እንዲሆን ከቅዱስ ቁርባን በኋላ ይዘመራል። ከዚህም ሌላ የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ከሕጽበተ እግር ሥርዓት በኋላ ሕዝቡ ከቄሱ ጋር መዝሙር 150ን እየዘመረ የዚያን ምሽት ታሪክ ያስታውሳል (አንቀጽ 122)።






















ጌታችን ከሐዋርያት ጋር አብሮ መዘመሩ በአዲስ ኪዳን ለሁላችንም አርአያ ለመሆን ነው። ዛሬ በዓለም ላይ ወደ መከራ ሲሄድ እያለቀሰ እንጂ እየዘመረ የሚሄድ ብዙ የለም። ዛሬ በስንብት ጊዜያችው በሰላም እንኳን ቢለያዩ እየዘፈኑ በሥጋዊ ሥርዓት የሚሰነባበቱ ብዙ ሰዎች ናቸው። ክርስቲያን ግን በማንኛውም የስንብትም ሆነ መንፈሳዊ ፍቅርን በሚገልጽ ፕሮግራም ላይ በየምክንያቱ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባዋል።

























3) የወኅኒ ቤት መዝሙር

ይህን መዝሙር የዘመሩት ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ሲላስ ናቸው። የዘመሩትም በወንጌል አገልግሎት ምክንያት በደረሰባቸው መከራ ተደብድበው ከቆሰሉ በኋላ በወኅኒ ተጥለው ከግንድ ጋር ተጠርቀው ሳሉ ነበር። በዚያ የመከራ ሰዓት ቁስላቸው ሳይሰማቸው እግዚአብሔርን በዜማ አመስግነውታል። የሚዘምሩትም ከጸሎት ጋር ነበር። መዝሙራቸው በንባብ ሳይሆን በዜማ ስለነበር በመንፈስም ስለነበር የሌሎችን እስረኞች ልቡና ይስብ ነበር። እስረኞችም ያደምጧቸው ነበር። እንዲያውም በመዝሙሩ የተነሳ አንዳንድ ታአምራት በመታየታቸው ይጠብቃቸው የነበረውን ዘበኛ እንኳን ከነቤተሰቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አሳምነው ለማዳን አብቅተውታል። ዘበኛውም በእግዚአብሔር ስላመነ ከነቤተሰቦቹ ጋር ሐሴት አድርጓል። ምናልባትም ደስታቸውን የገለጡት በመዝሙር ሊሆን ይችላል (ሐዋ16፥25-34)።

ከዚህም የምንረዳው መዝሙር በወንጌል አገልግሎት ውስጥ የነበረውን ኃይል ነው። ዛሬም ቢሆን ቃሉን በቀጥታ ብንነግራቸው ለማይገባቸውና ለማይቀበሉን ሰዎች አስቀድመን ስለ እነርሱ እየጸለይን ብንዘምር ምናልባት ልንስባቸው እንችላለን ። ከዚህም ሌላ መዝሙር ስናስደምጣቸው በመዝሙር ዉስጥ ልናስተምርቸውና ልንሰብካቸው ይገባናል። ዛሬ ብዙዎቻችን መከራ ሲደርስብን እናማርራለን እንጂ እንኳን በዜማ በግጥም በቃላትም አናመሰግነውም። ብናመሰግንም ብንዘምርም ከጸሎት ጋር ስላልሆነ የከንፈር ልማድ ብቻ ሆኖ ይቀራል። ነገር ግን መዝሙራችን እስራትን እስከ መበጠስ፣ መሰረትን እስከ ማናወጥ፣ የታመሙትን እስከ መፈወስ ድረስ ኃይል ይኖረዋል። እንዲህ ከሆነ የኑሮና ኃጢአት እስረኞች የሆኑትን ብዙ ሰዎች ተቃዋሚዎቻችን እንኳ ሳይቀር የጌታ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል።

4) የማኅበር መዝሙር

የማኅበር መዝሙር ስንል በአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች በማኅበር የሚዘምሩትን መዝሙር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ "በምትሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ መዝሙር አለው ትምህርት አለው . . . ሁሉ ለማነጽ ይሆናል" ብሏል (1ኛ ቆሮ 14፥26)። እንደገናም "በመዝሙርና በዝማሬ መንፈሳዊም ቅኔ እርስ በእርሳችሁ ተነጋገሩ። ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ" ይላል (ኤፌ 5፥19, ቆላ 3፥16)። እነዚህ ጥቅሶች የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በማኅበር ሲሰበሰቡ ይዘምሩ እንደነበር ያስረዱናል። ከዚህ በፊት የተመለከትናቸው የሆሳዕናው መዝሙር፤ የምሴተ ሐሙስ መዝሙር በማኅበር የተዘመሩ ናቸው። ጳውሎስና ሲላስም በእስር ቤት ሳሉ በዜማ እግዚአብሔርን ማመስገናቸው በዚያም ዘመን በክርስቲያኖች ዘንድ መዝሙር ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳለው የሚያስረዳ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ጥቅስ ሆነው የቀረቡ አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች የኅብረት መዝሙሮች እንዳሉም የሚናገሩ አሉ። ለምሳሌ (ኤፌ 5፥14)።












ከዚህም ሌላ በአዲስ ኪዳን የምናየው በዮሐንስ ራዕይ ስለ ማኅበር መዝሙር የተገለጸውን ይሆናል። ይኸውም አራቱ እንስሶችና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች (ኪሩቤልና ሱራፌል) እልፍ አእላፍ መላእክትን በሰማይና በምድር ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ የተለያየ አዲስ ቅኔ እንደዘመሩ የሚገልጽ ነው (ራዕይ 5፥6-14)። ይህም በማህበር ሆነው የዘመሩት ሲሆን የመዝሙሩ ዋነኛ መልእክትም ስለታረደው በግ የሚያወሳ ነው። ሲዘምሩም በገና እንደሚይዙ በታላቅ ድምፅም እንደሆነ ይገልጣል። በሌላ በኩል ደግሞ በአውሬውና በምስሉም በስሙም ቁጥር ላይ ድል የነሱት የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ በኅብረት ሲዘምሩ በራዕይ እንዳየ ዮሐንስ ከነመዝሙሩ ጽፎልናል (ራእይ 15፥2-4)።












በማንኛውም መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የማኅበር መዝሙር ዛሬም ቢሆን ትልቅ ቦታ ሊኖረው ይገባል። በመዘምራን እየተዘመረ ማኅበሩ በመንፈስ ሊያዳምጥ ይችላል። የመዝሙር ጸጋ ያለው አንድ ሰው በአዲስ ቅኔ እየዘመረ ማኅበሩ ሊሰማው ይችላል። ከዚህ ሁሉ የሚበልጠው ግን ማኅበሩ በአጠቃላይ በአንድ መንፈስ በታላቅ ድምፅ በተሰበረ ልብ መዘመር ሲችል ነው። እኛ ክርስቲያኖች ከኪሩቤልና ከሱራፌል ጋር እንዲሁም ከአእላፍ አእላፋት መላእክት ጋር ኅብረት አለን። ስለሆነም ከእነርሱ ጋር በአንድ ድምፅ ሆነን ስለታረደው በግ ልንዘምር ይገባል። ያለዚያ ግን ይመጣል የተባለው የዓመፅ ሰው የአውሬው መንፈስ ድል ሊነሳን ይችላል። ይህ እንዳይሆን ግን ከአሁኑ የአውሬውን ፍላጎትና መንፈስ ድል ነስተን እንደ እነዚያ ቅዱሳን አምላካችንን በዝማሬ እያመሰግንን ልንኖር ይገባል።

                       መዝሙር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በጥንታዊ ቋንቋችን በግእዝ በተዘጋጀው መዝሙር እጅግ የበለጸገች እንደሆነ ለዓለም የታወቀ ታሪክ ነው። የዚህ መዝሙር ደራሲ የሆነው ቅዱስ ያሬድ የተባለው የቤተክርስቲያናችን አባት ነው። ከዚህም አስቀድመን ግን ከቅዱስ ያሬድ በፊት መዝሙር በኢ/ኦ/ተ/ ቤተክርስቲያን እንዴት እንደነበር እንመለከታለን።











ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ።

ከቅዱስ ያሬድ በፊት መዝሙር በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ከቅዱስ ያሬድ በፊት ስለነበረው የመዝሙር ሁኔታ እስካሁን እርግጠኛ ታሪክ አልተገኘም። ነገር ግን በብሉይ ኪዳን ከሌዋውያን ጋር ወደ አገራችን የገባ እንደመሆኑ መጠን ልክ በእስራኤል በዳዊት ሥርዓት ይዘመር እንደነበር በአገራችንም ይዘመር ነበር ተብሎ ሲገመት ወደ እውነት የቀረበ ይሆናል። ከዚህም ሌላ መዝሙረ ዳዊትን ቀስ ተብሎ በንባባዊ ዜማ ይዘመር ነበር እንጂ፤ በዚያን ጊዜ ድምፅን ከፍ አድርጎ መዘመር እንዳልነበረ በቤተክርስቲያን ትውፊት ታሪክ ይናገራል።

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲስ ኪዳን የተሻገረች እንደ መሆኗ መጠን በሌዋውያን ሥርዓት የአዲስ ኪዳን መዝሙር ልንዘምር እንችላለን። በተለይም በዮሐንስ ራዕይ ላይ የተገለጠው የዚህ ዓይነት አዘማመር ነው። ንባባዊ ዜማም እንደተዘመሩ ያህል በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል። ዛሬ ግን ድምፃቸው ተለይቶ እንዲሰማ በመጮኽ፣ ከሚያዜሙና ከሚዘምሩት ውስጥ በዜማና በድምፃቸው የሚመኩ ስሜታዊያን ጥቂቶች አይደሉም። ነገር ግን በተለይም ድምፃቸው የማይታዘዝላቸውና የልሳን ወይም የአንደበት ችግር ያለባቸው ሰዎች በቀስታ በንባባዊ ቢያመሰግኑት በዜማ ከቀረበው መዝሙር እኩል ይቀበልላቸዋል። እግዚአብሔር የሚያየው ዋናው ነገር በተሰበረ ልብ የቀረበለትን ምስጋና ነውና።

ቅዱስ ያሬድ

ያሬድ ማለት በዕብብራውያን ቋንቋ "መውረድ" ማለት ነው። በብሉይ ኪዳን የሄኖክ አባት በዚህ ስም ተጠርቶ ነበር (ዘፍ 5፥18)። ታላቁ ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ያሬድ ይኖር የነበረው በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት ነበር። የተወለደውም በትግራይ ክፍለ ሃገር በአክሱም ከተማ ሲሆን ዘመኑም በ505 ዓ.ም. ሚያዝያ 5 ቀን ነው። አባቱ ይስሐቅ የሚባል ሲሆን እናቱ ደግሞ ክርስትና ትባል ነበር።

ቅዱስ ያሬድ የተማረው የአክሱም ገበዝ ከነበረው የእናቱ ወንድም ከሆነው ከአጎቱ ከጌድዮን ዘንድ ነበር። ከመዝሙረ ዳዊት ጀምሮ መኃልየ ነብያት፣ መኃልየ ሰሎሞንን፣ የመጻሕፍትን ትርጓሜ ብሉይ ኪዳንንና የሌሎችንም መጻሕፍት ቁጥራቸውንም አውቆ በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን በዲቁና ሲያገለግል ይኖር ነበር። ከሃያ አምስት ዓመት እድሜው በኋላ በመምሩ እግር ተተክቶ የመጽሐፍ መምህር ሆኖ ስለነበር ቅዱስ ያሬድ በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ጊዜ ሊቀ ካህናት ከነበረው ከእንበረም ወዲህ አራተኛ የመጽሐፍ መምህር ሆኖ ተቆጥሯል።










ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዝማሬ ንጉሡን ሲያስደምም።

ቅዱስ ያሬድ ይህን ያህል በቅዱሳት መጻሕፍት ሊቅ ስለነበር ያዘጋጃቸው የዜማ ድርስቶች ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር የሚስማሙና የተውጣጡ ናቸው። ድርሰቱንም ያዘጋጀው በሥርዓት ሲሆን በአራቱ ክፍል ዘመናት እንዲነገር አድርጎ ነበር። ንጉሡ አጼ ገብረ መስቀል በቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰት ተደንቀውና ተመስጠው የቅዱስ ያሬድን እግር ወጉት። ድርሰቱንም እንዲቀበሉ ለካህናቱ ሲነግሯቸው በዚያን ጊዜ የነበሩት ካህናት በምቀኝነት አንቀበልም ብለው እንደነበርና ምህላ ተይዞ ጌታ በራዕይ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ ሆኖ ለሕዝቡ በመታየቱ ምክንያት እንደ ተቀበሉት በቤተክርስቲያን ትውፊት ይነገራል። ቅዱስ ያሬድ ድርሰቱን ያዘጋጀው በ540-560 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

ይህ የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ሳዊራ፣ መንክር፣ እስክንድራ፣ በድር የተባሉ አራት ደቀ መዛሙርት ነበሩት። እነዚህን ደቀ መዛሙርቱን አስከትሎ እንደ ጣና፣ ጋይንት የመሳሰሉትን የተለያዩ የአገራችንን ክፍሎች እየጎበኘ ዜማውን እንዳስተማረ ታሪኩ ያስረዳል። ስለ ውጪውም ዓለም ቢሆን ቅዱስ ያሬድ እንግዳ አይደለም ። ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አባ ጰንጠሌዎንን ስለ ውጪው አገር ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ባሕል እየጠየቀ ከማወቁም በላይ ከአንዴም ሁለቴ ወደ ውጪ ሃገር ሄዶ በመጎብኘት ዓለም አቀፋዊ መረዳት የነበረው አባት እንደነበር ከታሪክ እንረዳለን። ቅዱስ ያሬድ ምድራዊ ሕይወቱን ፈጽሞ ያረፈው ግንቦት 11 ቀን 571 ዓ.ም. ነው። (ተሰወረ የሚል ታሪክም በቤተክርስቲያችን አለ።)

የቅዱስ ያሬድ ትምህርት ለዚህ ዘመን ትውልድ ሊደርስ የቻለው ቅዱስ ያሬድ ለደቀ መዛሙርቱ በማስተማሩ ነው። ደቀ መዛሙርቱ እየተማሩና እየሰፉ ለተከታዮቻቸው በማስተማር አስተላልፈውልናል። ሆኖም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዮዲት እና በግራኝ መሐመድ ጊዜ ስትሰደድ ሊጠፋ እንደተቃረበ እንደገናም በእግዚአብሔር ፈቃድ ትንሣኤ በማግኘት እስከ ዘመናችን ሊደርስ ችሏል።

እኛም መንፈሳዊ ልጆቹ ታሪክን በመተረክ ብቻ ሳንወስን መዝሙሩንና አዘማመሩን በማወቅ እግዚአብሔርን ልናመሰግንበት ይገባል። በተለይም በአሁኑ ጊዜ ይህ መዝሙር ከነዜማው በአማርኛ ቋንቋ ተዘጋጅቶ ለሕዝቡ ቢደርሰው ወይም ሁሉም ግዕዝን የሚያውቅበት ዘዴ ቢፈጠር ታሪኩ ከመጠበቁ ጋር ሕዝቡ ትርጉሙን እያወቀ ከካህናቱ ጋር አብሮ መዘመር ይችል ነበር። ምእመናን ከዳር ሆነው በተመስጦ መዘመር እየፈለጉ ስለማያውቁ ይቸገራሉ። ዛሬ በየሰንበት ትምህርት ቤቱም ቢሆን በአማርኛ ቋንቋ በአብዛኛው የሚዘምሩ መዝሙሮች በአንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ጥረት የተደረሱ አዳዲስ መዝሙሮች ናቸው። ይህ የሚደገፍ እንጂ የሚነቀፍ ባይሆንም የቅዱስ ያሬድን መዝሙር ከነዜማው ለምእመናን በሚገባቸው በአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅቶ የሚያቀርብላቸው ዳግማዊ ያሬድ ለቤተክርስቲያን ዛሬም ያስፈልጋል።

አምስቱ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቶች

ቅዱስ ያሬድ የደረሳቸው የሁሉ የሆኑት አምስት የድርሰት ዓይነቶች የሚከተሉት ናቸው።

ሀ) ድጓ              ለ) ጾመ ድጓ        ሐ) ዝማሬ           መ) መዋስዕት                   ሠ) ምዕራፍ

ከእነዚህ ሌላ አንቀጸ ብርሃን የሚባል ድርሰት የቅዱስ ያሬድ ድርሰት እንደሆነ ታሪክ ያስረዳናል። ቅዱስ ያሬድ የራሱን ድርሰት ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ድርስቶች ለምሳሌ ውዳሴ ማርያምን፣ አሥራ አራቱን ቅዳሴ ዜማ እንዳወጣላቸው በትውፊት ይተረካል። ከዚህ ቀጥለን አምስቱን የቅዱስ ያሬድን ድርሰቶች በየተራ እንመለከታለን።

1ኛ) ድጓ

ድጓ ማለት ልቅሶ (ሙሾ) ማለት ነው። ይኸውም መዝሙር ሐዘን ነው። ድጓ በአራት ታላላቅ ክፍሎች ይከፈላል። እነርሱም፥

           1) ዮሐንስ ምድቡ ከመስከረም 1 እስከ ኅዳር 30 ቀን

           2) አስተምህሮ ምድቡ ከታህሳስ 1 እስከ መጋቢት 30 ቀን    

           3) ጾመ ድጓ ምድቡ በወርኃ ዓቢይ ጾም             

           4) ፋሲካ ምድቡ ከሚያዚያ ወይም ከትንሳኤ እስከ ጳጉሜ መጨረሻ

2ኛ) ጾመ ድጓ

ይህ ክፍል እዚህ ላይ ራሱን ችሎ ቢቀርብ ሦስተኛው የድጓ ክፍል ነው። ቃሉ እንደሚያመለክተው ይህ ክፍል የሚዘመረው በወርኃ ጾም ነው። መዝሙሩንም በነግህ፣ በሠለስት፣ በቀትር፣ በሠርክ እንዲሁም በሌሊት እንዲዘመር ሆኖ የተዘጋጀ ነው። በውስጡም ያለው ፍሬ ሃሳብ የጾምና የጸሎትን ጠቃሚነት የሚያስተምርና ታላቅ ምስጢር ያለው ነው። የተማሪዎችም የመጀመሪያው የትምህርት ደርጃቸው ጾመ ድጓ ነው።

3ኛ) ዝማሬ

ዝማሬ ማለት እንደ መዝሙር ሁሉ ምስጋና ነው። ዝማሬ የማህበር ምስጋና ሲሆን የሚዘመረውም በቅዳሴ ጊዜ ከድርገት በኋላ ነው። ይኸውም ጌታችን ሐዋርያት በምሴተ ሐሙስ ከሥጋ ወደሙ በኋላ መዘመራቸውን መሰረት በማድረግ የሚዘመር ምስጋና ነው። ቅዳሴው ዕዝል ከሆነ ዝማሬውም በዕዝል ዜማ በመቋሚያ ብቻ ይዘመራል። ቅዳሴው ግዕዝ ከሆነ ግን ያለ መቋሚያ በአንድ ወይም በሁለት መዘምራን እየተቀኘ በብዙዎች መዘምራን ድምፅ እየታጀበ በግዕዝ ዜማ ይዘመራል። ዝማሬ በሦስት ይከፈላል። እነርሱም፥

1) ዝማሬ            2) አኮቴት                      3) ምስጢር ናቸው።

4) መዋስዕት

መዋስዕት ማለት ምልልስ ማለት ነው። በግራና በቀኝ እየተመላለሰ የሚዘመር መዝሙር ነው። በውስጡ ስለ ጌታ፣ ስለ እመቤታችን፣ ስለ ጻድቃንና ስለ ሰማእታት፣ ስለ ደናግልና መነኮሳት፣ እና ስለ ቅዱሳን መላእክት ከመናገሩም በላይ ስለ ሙታን ፀአተ ነፍስና እረፍተ ነፍስ በስፋት ይዟል። ስለዚህ ይህ መዝሙር በአብዛኛው የሚዘመረው ለሙታን በሚደረገው በጸሎተ ፍትሐት ላይ ነው። ሆኖም በጌታና በእመቤታችን፣ በመላእክትና በጻድቃን ሰማእታት በዓል ላይም በአገልግሎት ይውላል። መሥዋዕት ከዝማሬ ጋር የሚሰጥ ትምህርት ሲሆን ምንም ዓይነት የውስጥ አከፋፈል የለውም።

5ኛ) ምዕራፍ

ምዕራፍ ማለት ማረፊያ ማለት ነው። የዜማውን ማሳፈሪያ የሚነግረን ስያሜ ነው። የምዕራፍ ትምህርት አሰጣጥ እንደ ሌሎች የያሬድ ድርሰቶች መጽሐፍ ዘርግቶ ሳይሆን በውስጡ ያሉትን ትምህርቶች በቃል በማጥናት የሚሰጥ ነው። የምዕራፍ ድርሰት መስተጋቦዕ፣ አርባዕት፣ አርያም፣ ሠለስት፣ መወድስ፣ ስብሐት ነግህ እያለ የሚሄድ የውስጥ አከፋፈል አለው። በአጠቃላይ ግን ምዕራፍ በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ይከፈላል። እነርሱም፥

1. የዘወትር ምዕራፍ፥ በዓመት ውስጥ ባሉ ሳምንታትና በዓላት ወቅትን ጠብቆ የሚዘመር፣

2. የጾም ምዕራፍ፥ በዓብይ ጾም የሚባል ነው።

ማስገንዘቢያ ፥ ቅዱስ ያሬድ በሕይወት ዘመኑ ትምህርትና ጸሎት ምስጋናም የሆኑትን እነዚህን የመዝሙር ድርሰቶች በጽሑፍ ትቶልን አልፏል። ዛሬ ግን እንኳን አዲስ ድርሰት በቤተክርስቲያን ልናበረክት ቀርቶ ያለውንም አጥንቶ ለመዘመር ብዙዎቻችን አልቻልንም። ስለዚህ የግዕዙን ቋንቋ አውቀን እነዚህን የያሬድ ድርሰቶች አጥንተን ለመዝሙራችን ድርሰቶች ምንጭ በማድረግ እየተረጎምን ለሕዝቡ የሚሆን የአማርኛ መዝሙሮችን ማዘጋጀት ይገባናል።

ማኅሌት (አቋቋም)

ማኅሌት የሚለው ቃል ኅላየ ከሚለው ግሥ የተገኘ ቃል ነው። ኅላየ ማለት ዘፈነ ማለት ስለሆነ፤ ማኅሌት ማለት ደግሞ ዘፈነ ማለት ነው። ሆኖም ይህ ቃል መንፈሳዊ ምስጋናን እንጂ ዓለማዊ ዘፈንን አያመለክትም። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ማኅሌት በመቋሚያ፣ በከበሮና በጽናጽል በዓብይና በንዑስ መረገድ፣ በወረብ የሚዘመረውን መዝሙር ክንውን የሚገልጽ ሲሆን፣ አቋቋም የሚባለው ግን የአንድ የዜማ ስልት መጠሪያ ነው።

ታሪካዊ አመጣጡ በአጭሩ

ማኅሌት እንደ አሁኑ ይዞታ ሳይሆን ወደ ቁሙ ዜማ በማስጠጋት ከቅዱስ ያሬድ ጀምሮ የነበረ ነው። ነገር ግን ደረሰው የሚባለው በጎንደር ዘመነ መንግሥት የነበረው ባሕታዊ ኤስድሮስ የሚባለው ሊቅ ነው። ላህይና ቃናው እየተሻሻለ ሲመጣ የቻለው ደግሞ በአፄ አድያም ሰገድ (1665 እስከ 1689 ዓ. ም.) ዘመን ነው። ለዝማሜና ለመረግድ፣ ለከበሮና ለጽናጽል እንዲመች ሆኖ የአቋቋም ባሕልና ሥርዓት ከበፊቱ በበለጠ የተሻሻለው በአፄ በካፋ ዘመን በመሪጌታ መብረቁ፣ በመሪጌታ ነጎድጓድ፣ በእነ ጸሐፊ ትዕዛዝ ድሜጥሮስ በተባሉት ሊቃውንት አማካይነት ነው። ወንበር ዘርግቶ ማስተማር የጀመረው ግን በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት 1882 ዓ.ም. ከድርቡሾች ጥፋት በኋላ የአማረ እሸቱ ተማሪ በነበሩት በመሪጌታ ላቀው ፈለቀ አማካይነት ነው። ሆኖም መሪጌታ ላቀው ፈለቀ ከትምህርት ጓደኛቸው ከመሪጌታ ገብረ ዮሐንስ ጋር ወዝ በመለዋወጥና ይትብሐል በማሻሻል ተለያይተዋል።

ከዚህ ጀምሮ በየጊዜው በሚነሱት መምህራን አማካይነት ወዙና ልህዩ እየተለያየ መጥቶ የላይ ቤት፣ የታች ቤት፣ ሳንኳ፣ ጎንደሬ፣ ተክሌ የሚባለው ልዩነት ሊፈጠር ቻለ። ሆኖም ልዩነቱ የአዘማመሩና የአቀራረቡ ሁኔታ ስለሆነ ብዙ የጎላ ልዩነት ነው ለማለት አይቻልም። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ሁሉንም አስተባብሮ የያዘ የእርቅ ቤት የሚባል አቋቋም አለ።

ሥርዓተ ማኅሌት

በዚህ ክፍል የማኅሌት ቅደም ተከተሉን አፈጻጸሙን እንመለከታለን። እያንዳንዱንም ሥርዓት ምስጢራዊ ትርጉም ያለው በተለይም የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ የሚያሳይ ሥርዓት እንደሆነ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ይናገራሉ።






















ማሕሌተ ጽጌ በሚዩኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል።

ቅደም ተከተሉ፥

1. ካህኑ አስርቆት አድርጎ በጸሎት ይጀምራል።

2. ሚካኤል ሊቀ መላእክት ሰአል በእንቲአነ የሚለውን እየተቀባበሉ ይባላል።

3. ካህኑ አቡነ ዘበሰማያት ይላል።

4. "ስምዐኒ እግዚኦ ጸሎትየ" በመሪና በተመሪ በአንሺ ይባላል።

5. "ስቡሕ ወውዱስ ዘሣረረ ኩሎ ዓለም በአሐቲ ቃል" የሚለውን ምስጋና ይባላል።

6. ነግሥ ይባላል በዚህ ውስጥ ከመልክአ ሥላሴ ገብቶ የሚባል አለ።

7. "ዘመንክር ጣዕሙ" ከተባለ በኋላ ከበዓሉ ነግሥ ይባላል።

8. ከዚህ በኋላ እንደየ በዓሉ መልክአ መልክዕ ይባላል።

9. ከሚመረገዱት መልኮች ቀጥሎ ዚቅ ይገባል ወረብ ይወረባል።

10. መልክእ ካለቀ በኋላ ካህኑ አቡነ ዘበሰማያት ይላል።

11. ከዚያም ተመሲሊኪ ይባልና እንደገና አቡነ ዘበሰማያት ይሰጣል።

12. ስንክሳር ይነበባል።

13. አርኬ ይደረሳል።

14. መልክአ ውዳሴ ይባላል።

15. ምስባክ ይባላል።

16. ምልጣን እስመ ለዓለም ይባላል።

17. የኪዳን ሰላም ሰልም ተብሎ ኪዳን ይደርሳል።

18. እንደ ትእዛዙ አቡን ወዝም ዕዝል ይባላል።

19. በመጨረሻም አራራይ፣ ሰያም ተጸፍቶ ጸሎተ ኑዛዜ ተሰጥቶ ቅዳሴው ይቀጥላል።

ይህ ሁሉ ሥርዓት የሚፈጸመው፥

1) በቁም ዜማ                  2) በዓብይና በንዑስ መረግድ             3) በአጽሕሶ (በሽብሸባ)

4) በጽፍዐት                    5) በመሪና በተመሪ በአንሺ ነው።















ወረብ በመስቀል አደባባይ።












የላሊበላ ካሕናት በሽብሸባ ምስጋና ለፈጣሪ ሲያቀርቡ።

የመዝሙር ግጥምና ዜማ

አንድ መዝሙር ልብ የሚመስጥ የሚያደርገው የግጥምና የዜማ ጥራት ነው። ምንም እንኳን እግዚአብሔር የአንድን መዝሙር የሥነ ግጥም የዜማ ሁኔታ ባይመለከትም ክርስቲያኖች ሁሉም ነገር የተሟላለት (የተዋጣለት) መዝሙር ለእግዚአብሔር ማቅረብ ይገባቸዋል። በእርግጥ ያለ ግጥም በስድ ንባብም ማዜም ይቻላል። አብዛኛውን ጊዜ መዝሙር በግጥም የሚዜም ሆኖ እናገኘዋለን። ስለዚህ መዝሙሮችን ለማዘጋጀትም ሆነ የተዘጋጀውንም በተረዳ አእምሮ፣ በተሰበረ ልብ ለመዘመር የግጥምንና የዜማውን ፀባይ ማወቅ ያስፈልጋል።

ሀ. የመዝሙር ግጥም

ግጥም ማለት በፊደል፣ በቃል ወይንም በምስጢር የገጠመ የስንኞች ድርደራ ነው። ከመዝሙረ ዳዊት ሌላ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጽሐፈ ኢዮብ (ከምዕራፍ 3 እስከ 41)፣ መጽሐፈ ምሳሌ የመሳሰሉት መጻሕፍት በዕብራይስጡ ቋንቋ በግጥም የተጻፈ ከመሆናቸውም በላይ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተመዘገቡት መዝሙሮችም በግጥም የተዘመሩ ናቸው (1ኛ ሳሙ 2፥1-10፣ 1ኛ ዜና 16፥8-36፣ ሉቃ 1፥46-55፣ ሉቃ 1፥68-79 . . . ወዘተ)።

በግጥም ውስጥ ያሉት ሁለት ክፍሎች በሐሳብ ወይም በአቀራረብ በሦስት መንገድ ይታያሉ። ይኸውም፥

1. ሁለተኛውም ለመጀመሪያው አስረጂ በመሆን የመጀመሪያውን ሐሳብ እየተደገፈ የሚገጠም ግጥም ነው።

ለምሳሌ፥  ምድር ሞላዋ የእግዚአብሔር ናት፤

                       ዓለምም በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ።

                       እርሱ ባባሕሮች ላይ መስርቷልና፣

                       በፈሳሾችም ላይ አጽንቷልና። (መዝ 23፥1-2) ይላል።

ይኸውም ባሕርን በመመስረቱና በፈሳሾች ላይ በማጽናቱ ምክንያት ምድርና መላዋ ዓለምም በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ናት ማለት ነው።












2. የሁለተኛው ሐሳብ ለአንደኛው የግጥም ክፍል ሃሳብ ተቃራኒ ሆኖ የሚቀርበም የግጥም ዓይነት አለ።

   ለምሳሌ፥        ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉ፣ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። (መዝ 36፥9) ይላል።

በዚህ ግጥም እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ምድርን የመውረሳቸው ሐሳብ ክፉ አድራጊዎች ለመጥፋታቸው ሐሳብ "ግን" በሚለው አፍራሽ ቃል ተቃራኒ ሆኖ ቀርቧል። በዚህም የእግዚአብሔርን ፍርድ አድንቆ ዘምሯል።

 3. ከሁለቱም የግጥም ክፍሎች ያሉ ባለቤቶችንና ተሳቢዎች ግሦችን ሌችም የሚገናኙበትና ምስጢር  

 የሚብራራበት ግጥም አለ።

ለምሳሌ፥ የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው ልብን ደስ ያሰኛል፣

                       የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ቡሩህ ነው ዓይንንም ያበራል። (መዝ 18፥8) ይላል።

"የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው" የሚለው "ልብን ደስ ያሰኛል" ከሚለው ጋር የእግዚአብሔር ትዕዛዝ "ቡሩህ" ነው የሚለው ዓይንንም ያበራል ከሚለው ጋር በሥነ ጽሑፍና በሚስጥር የተስማማና የተገናኘ አባባል ሆኗል። ከዚህም ሌላ ግጥም ሊስተዋል እንዲችልና ሲዘምሩትም እንዳያስቸግር ዜማ መስበር የለበትም።

የአንድ መዝሙር ግጥም ልክ እንደሰበሰቡት መልእክቱን የተከተለ ርዕሱን የተበቀ ሊሆን ይገባዋል። በቅኔ መንገድ ቢቀርብ በበለጠ ጥሩ ይሆናል። በአዝማች ወይም ያለ አዝማች በቁሙ እንዲባል ሆኖ ሊዘጋጅ ይችላል። በቤተክርስቲያናችን የነግስና የመልከእ አቀራረብ በግጥም የተዘጋጀ ነው። መዝሙር ምስጋና ብቻ ሳይሆን ትምህርትም በመሆኑ ግጥሙ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚስማማ ለትምህርትና ለተግሣጽ የሚሆን ስለ እግዚአብሔር ገናናነት ስለተደረገልን ነገር የሚመሰክር በተለይም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የማዳን ሥራ የምንመሰክርበት ሊሆን ያስፈልጋል።

መዝሙር እንዴት መዘመር አለበት?

ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ "በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው ይላል (1ኛ ቆሮ 14፥26)። ደግሞም በመዝሙርና በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ ይላል (ቆላ 3፥16, ኤፌ 5፥19)። እንዲህ ከሆነ ክርስቲያኖች ለአምልኮትም ሆነ ለወንጌል ስብከት በቤቲክርስቲያን ሲሰበሰቡ እንዲሁም በማኅበር እና በግል መዘመር አለባቸው። ነገር ግን ክርስቲያኖች ሲሰበሰቡ ለእያንዳንዱም መዘመር ለእያንዳንዱም ትምህርት አለውና መዝሙር የጸጋ ስጦታቸው የሆነ ተሰባስበው መዘምራን በመሆን ሊያገለግሉ ይችላሉ። ቅዱስ ዳዊት በመገናኛው ድንኳን እንዲያገለግሉ ያደራጃቸው መዘምራን ነበሩ (2ኛ ዜና 29፥25-28)። ወንዶችም ሴቶችም መዘምራን መሆን ይችላሉ። የጾታ ልዩነት የለም። ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ከተመለሱት እስራኤላውያን ሁለት መቶ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ነበሩ (ዕዝ 2፥65-66)። በዚህ መሰረት ቤተክርስቲያን የካህናት መዘምራን አሏት። እንዲሁም በየሰንበት ትምህርት ቤቱ ቋሚ የወንዶችና የሴቶች መዘምራን አሏት።

በመዘምራን ስለሚያገለግሉ

በአጭሩ ስለ መዘምራንና ስለ መዝሙር ይህን ያህል ካየን አሁን ደግሞ "መዝሙር የሚዘምሩት ሰዎች እንዴትና ምን መሆን አለባቸው?" የሚለውን የመዘምራንን ነገር እንመልከት።

መዘምራን ከመዘመራቸው በፊት የመዝሙርን ምንነት ማወቅ ዜማን ብቻ ሳይሆን ቃሉን ማስተዋል ለምን (ለማን) እንደሚዘምሩ ማወቅ ዘምረው ምን እንደሚያገኙ መረዳት አለባቸው።

የመዝሙርን ምንነት ያላወቀ ዘማሪ መዝሙር ጊዜ ማሳለፊያ ወይም መዝናኛ ሆኖ (መስሎ) ሊታየው ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሰው በመዘምራን መካከል ካለ መዘምራን ተገንዝበው የሚዘምሩት መዝሙር ሌሎች እንዳይድኑበት እንቅፋት ሊሆን ይችላል፤ ይሆንማል። መዝሙርን መጀመሪያ ያስተማረው እግዚአብሔር ነው ሰው አይደለም። ማንኛውም ዘማሪ በሚዘምርበት ጊዜ ያንን መዝሙር እግዚአብሔር በአፉ ውስጥ እንዳስቀመጠለት መገንዘብ አለበት።

ዘማሪው እንደዘፈን የሚቆጥረውና ያልተረዳው ከሆነ የሚዘምረው መዝሙር ሰዎችን በፍቅረ እግዚአብሔር የሚያጠምድ አይሆንም። የሚዘምረውን መዝሙር የማያውቅ ከሆነ እየዘመረ እንኳ ዓይኑ ይቅበዘበዛል፣ ሰውን ብቻ ይመለከታል፣ ዘሩ(ቃሉ) እና ዜማው ይደናገረዋል። ስለዚህ አገልግሎቱ ሰዎችን በማቅረብ ፈንታ ሰዎችን የሚገፋ ይሆናል። ዘማሪው ከዚህ ሁሉ እንዲድንና እንዲጠበቅ መዝሙሩን በሚገባ ማወቅ አለበት። ደግሞም ማወቅ ብቻ ሳይሆን በማን ፊት እንደሚዘምር መገንዘብ አለበት።

መዘምራን የምእምናንን ልብ ለእግዚአብሔር ቃል የለሰለሰ መሬት ለማድረግ በዝማሬ ማረሻ የሚያርሱ፣ የሚቀሰቅሱ እና የሚያለሰልሱ መሆን አለባቸው። በሚያሳዝነው መዝሙር ላይ የደስታ ፊት ገጽታ፣ በሚያስደስተው መዝሙር ላይ የሐዘን የትካዜ ገጽታ ሊታይባቸው አያስፈልግም። የሰውነታቸው ሁኔታ (እንቅስቃሴ) ከመዝሙሩ ጋር መሆን አለበት። በተለይ ግን መዘምራን የመድረክ ላይ ክርስቲያኖች ብቻ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ አለባቸው። በአሁኑ ሰዓት ትልቅ የቤቲክርስቲያን ችግር፤ የሰባኪያን እንደ ስብከታቸው፣ የመዘምራን እንደ መዝሙራቸው አለመሆን ነው። "ጹሙ ወጸልዩ ለእግዚአብሔር ተቀነዩ" ጹሙና ጸልዩ ለእግዚአብሔርም ተገዙ ብሎ ጠዋት የዘመረውን ከሰዓት ባኋላ ደግሞ ሲጾም ሲጸልይ ለእግዚአብሔር ሲገዛ አይታይም። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ዘማሪው የሚዘምረው ዜማውን ብቻ እንጂ ቃሉን ጭምር ስላልሆነ ነው። እግዚአብሔር ከዜማ በፊት የሚያየው የሚያዜመውን ሰው ሕይወት ነው። በዝማሬ የሚታለል (የሚሸነገል) አምላክ አይደለም። የመዘምራኑ የውስጥ ሕይወት ከመዘመራቸው በፊት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የለዘበ፣ የጣፈጠ እና ልዑል እግዚአብሔር ሕዝብን የሚባርክበትና የሚለወጥበት ልቦና ሊኖራቸው ይገባል። መዘምራን የድምፅ፣ የአለባበስ፣ የአቋቋምና የአፍ አከፋፈት ተወዳዳሪዎች መሆን የለባቸውም። ሱራፌልና ኪሩቤል የሚያመሰግኑትን ጌታ ለማመስገን ከእርሱም ጋር ለመነጋገር የተቀደሰ አንደበትና የተተኮሰ ከንፈር ነው የሚያስፈልገው (ኢሳ 6፥5-7)።

መዝሙር ለእግዚአብሔር በእርሱ ፊትና በእርሱ ቤት የሚዘመር ምስጋና ነው። በቤቱ የሚዘምር የተቀደሰ ሕይወት ነው። መዘምራን በሚዘምሩበት ጊዜ ከፊታቸው ሰማያዊ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ አለና በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ እንዲቆሙ ጊዜ ወስደው መጸለይ አለባቸው። ያለዚያ ግን በዚያ በእግዚአብሔር መድረክ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን ጋርደው እነርሱ ለመታየት የተዘረጉ መጋረጃዎች ይሆናሉ ማለት ነው። የእግዚአብሔር አገልጋይ ደግሞ ዓላማው የእግዚአብሔር ነፀብራቅ መሆን ስለሆነ እንደ መስታወት የእግዚአብሔርን ብርሃን የሚያንፀባርቅ ሕይወት ሊኖራቸው ይገባል።

አቤት! መዘመራቸው (አቤት! አሰላለፋቸው) ለመባል ብቻ መድረክ ላይ የሚወጡ መጎናጸፊያቸው ክርስቶስ ኢየሱስ ያልሆነ መዘምራን ለማኅበራቸውም ሳይቀር የውድቀት ምክንያት ይሆናሉ። ስለዚህ በአገልግሎታቸው ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ጎልቶ እንዲታይ በመዝሙራቸው ያዘኑ እንዲጽናኑ፣ የተሰበሩ እንዲጠገኑ፣ የተጠራጠሩ እንዲያምኑ፤ ዘወትር በፍቅርና በሰላም በመንፈስ በኅብረት በመጸለይ፤ የተጉ፣ የማይተማሙ፣ የማይኮራረፉ መሆን አለባቸው። እንዲህ ከሆነ የሚዘምሩት መዝሙር የእስር ቤት መሰረት የሚያናውጥ፣ ሰንሰለት የሚበጥስ፣ ነፍሳትን የሚያድን ይሆናል (የሐዋ ሥራ 16፥16-34)።

በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎች በመሪዎችና በነገሥታት ፊት ዘፍነውና ቦርቀው የሚሰጧቸው ጊዜያዊና ኃላፊ የሆነ የኃጢአት ውጤት ነው (ማቴ 14፥1-12)። ለእግዚአብሔር መዘመር ግን በምድር ሰላም እና የሕሊና ዕረፍት በመጨረሻም የዘለዓለምን ሕይወት ያቀዳጃል፣ ያወርሳል። ("አገልግሎት" በዲያቆን እንግዳ ቸሩ ገጽ 4-5)።

መዘምራን ልክ እንደ ወንጌል ሰባኪዎች እንደ ሌሎችም አገልጋዮች በክርስቲያኑ ሕዝብ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጣሉና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የታነጹና ለሌላው ብርሃን መሆን የሚችሉ እንዲሆኑ በጾምና በጸሎት ሊተጉ ይገባል።

 

ማጠቃለያ፥

ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ፣

ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ።

እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፣ በማስተዋል ዘምሩ። (መዝ 45፥5-6)።

እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ አምላክና ንጉሥ ነው። ስለዚህ ምስጋናውም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ነው። እግዚአብሔር በባሕርይው የተመሰገነ ነው። ስለዚህ ብናመሰግነውም የምንጠቀመው እኛ መሆናችንን ልናስተውል ይገባናል። እስካሁን ድረስ ስለ መዝሙር ያለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊና ትውፊታዊ ትምህርት አይተናል። ነገር ግን ይህ ትምህርት ስለ መዝሙር በጥልቀት እንድናዉቅ ሳይሆን በማስተዋል እንድንዘምር ለማድረግ የተሰጠ ትምህርት ነው።

መዝሙር በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ሃይማኖታዊ ፍቅር የሚገለጽበት መንገድ ነው። በእኛ ላይ ያለው ዓላማዊ ፍቅር ነው (መኃልየ 2፥4)። በላይ ቤትና በታች ቤት ዜማ በሌሎችም የዜማ ልዩነቶች እየተጣላንና እየተነቃቀፍን ጥዑም የሆነውን ማኅሌት ፍቅር አልባ ልናደርገው አይገባም። በየሰንበት ትምህርት ቤቱም በሚፈጠሩ የዜማ ልዩነቶች ምክንያት ፍቅርን በማደፍረስ እግዚአብሔርን እናመስግን ብንል የከንፈር ምስጋና ይሆናል። መዝሙሮች ሁሉ አንድ ወጥና ተመሳሳይ ያሬዳዊ ዜማ እንዲኖራቸው የሚመለከታቸው ሁሉ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። ከዚህም ሌላ እውነትንና እውነተኞችን እየተጸየፉና ደሃ እየበደሉ፣ ጻድቃንን እያስጨነቁ፣ ፍርድ እያጣመሙ፤ እግዚአብሔር ሁሉን እንደሚወድ ፍቅሩን ባለማስተዋል የሚዘመረው መዝሙር በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የለውም (አሞጽ 5፥23)። ስለዚህ ከዚህ ሁሉ ርቀን ለሰማያዊ ንጉሥ ለእግዚአብሔር በፍቅር የምንዘምር መሆናችንን ልናስተውል ይገባል።

አንዳንድ ጊዜ መዝሙር ሲዘመር ከመጠን በላይ ጩኸት ሲበዛ በስሜት በመነዳት ከሥርዓት ውጪ መሆን ይታያል። ይህ ማንን እንደምን አመሰግን፣ እንዴት እንደምን አመሰግን፣ ምን እያልን እንደምን አመሰግን ካለማስተዋል የተነሳ ነው። ስለዚህ የምንዘምረውን ምን እያልን እንደምን አመሰግን አምላክ እግዚአብሔርን በኪሩቤል ጀርባ ላይ እንዲሁም በመስቀል ዙፋን ላይ ሆኖ በዓይነ ልቦና እያየነው፤ በግላችንም ሆነ ከዓለም ጋር ያደረገልንን ውለታ እያስታወስን በማስተዋል ልንዘምር ያስፈልጋል።

የስብከታችን ማዕከል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ሁሉ የመዝሙራችንም ማዕከል እርዕስ ሊሆን ይገባዋል። ወደ ቅዱስ ያሬድ ከተላኩት ወፎች አንዷ " አዲሱን የእግዚአብሔር ምስጋና ሥራ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው" ብላ እንደ ነገረችው መረዳት ይኖርብናል (ያሬድና ዜማው ገጽ 23)። በመጽሐፍ ቅዱስም "በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት" የሚል ቃል ይገኛል (ቆላ 3፥16-17)። ስለዚህ ስሙን በትሕትና እየጠራን፣ እስከ መስቀል በደረሰ ፍቅሩ እንዳዳነን እያሰብን፣ በከንፈር ብቻ ሳይሆን በልብ በማስተዋል እንዘምርለት።

አንድ መዝሙር ታሪክ፣ ምስጢርና መልእክት ይኖረዋል። ይህም በመዝሙር ቃል ውስጥ ከላይ እስከ ታች ተያይዞ የሚገኝ ነው። ስለዚህ ዜማውን ወይም አዘማመሩን ብቻ ሳይሆን ታሪኩን፣ ምስጢሩንና መልእክቱ ምን እንደሆነ እያስተዋልን መዘመር አለብን። ቅዱስ ዳዊት "እዘምራለሁ ንጹሕ መንገድህንም አስተውላለሁ" ብሏል (መዝ 101፥2)።

ወስብሐተ ለእግዚአብሔር . . . አሜን።