Äthiopisch Orthodoxe Tewahedo Debre Bistrat St. Gabriel Kirchengemeinde München e.V.

በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሀዶ ቤተክርስትያን፣የሙኒክ ደብረ  ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን 

ሥርዓተ ቅዳሴ (ቅዳሴ ጸሎት)
ቅዳሴ በሥርዓተ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት በኅብረት የሚጸለይ የኅብረት ጸሎት ነው፡፡ ከጸሎቶች ሁሉ የላቀ የጸሎት ክፍል ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ 5ቱ ምሥዋዕቶች ተሟልተው ይገኙበታል። እዚህንም 5ቱን መሥዋዕቶች ማንኛውም ክርስቲያን ለፈጣሪው የሚያቀርበው ነው፡፡
ሥርዓተ ቅዳሴ (ጸሎተ ቅዳሴ)  1.የቁርባን መስዋዕት የሚቀርብበትና የሚሰዋበት እንዲሁም ምእመናን የሚቆርቡበት ብቸኛ የጸሎት ሥነ ሥርዓትጊዜ ነው። በዚህ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ክፍለ ጊዜ መስዋዕቱም በቤተልሔም ይዘጋጃል፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ በቤተ- መቅደስ ውስጥ ደግሞ ቀርቦ በአገልጋዮቹ በካህናት ጸሎት ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት ወይኑ ተለውጦ ደመ መለኮት የሚሆንበት የጸሎት ክፍለ ጊዜ ነው። ይህም ታላቅ ምስጢር የጌታችንን በቤተልሔም መወለድን፣ በቤተክርስቲያን በቤተ መቅደስ መፈተቱ፣ በቀራንዮ አደባባይ ለዓለም ድኅነት ብሎ የመሰዋቱንና ከእርሱ የበላና የጠጣ እርሱ የገባውን  ቃል ኪዳን ይፈጽማል፣ ያከናውናል።
2. ጸሎተ ቅዳሴ ካህኑ፣ ዲያቆኑና ሕዝቡ በመቀባበል በአንድነት ምስጋና ለፈጣሪያቸው የሚያቀርቡበት የከንፈራችን ፍሬ የሚሰዋበት የጸሎት ክፍል ነው፡፡
3. በቅዳሴ ጊዜ የሚበራው ጧፍ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የሚሠጥ የመብራት መስዋዕት ነው፡፡ ምሳሌነቱም የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው። ይህውም ጌታችን ጨለማ ለሆነ ዓለም ብርሃን ሆኖ ብርሃንን ሊያበራ ወደ ዓለም መቷልና ነው፡፡
4. ሥርዓተ ቅዳሴ የዕጣን መስዋዕት የሚቀርብበት ጊዜ ነው። የዕጣን ጸሎት ካህኑ ብቻ የሚያጥነው ሲሆን ይህውም በማዕጠንቱ አማካኝነት ቅዱሱን እጣን በመንበሩ፣ በቅዱሳን ሥዕላቱ፣ በሕዝቡ መካከል ያጥናል። ይህውም የሕዝቡን ጸሎት ወደላይ ወደ ሥላሴ መንበር ይዞ ይወጣል። በሰማይም ያሉ ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሥላሴን መንበር እንደሚያጥኑ ሁሉ በምድርም ያለው ካህን የሰማያዊው ምሳሌ ነውና በምድር ያለውን መንበር በማጠን ለእግዚአብሔር የዕጣን መስዋዕት ያቀርባል፡፡
5. ሥርዓተ ቅዳሴ የሰውነት መስዋዕትነት የሚቀርብበት ጊዜ ነው። ምክንያቱም አብዛኛውን ሰዓት ሙሉውን ማለት ይቻላል በመቆም የሚጸለይ የጸሎት ክፍለ ጊዜ ነው፡፡ በመሐል 2 ጊዜያት ብቻ የስገዱ ትዕዛዝ ሲተላለፍ ሕዝቡ ሁሉ ፊቱን ወደ ፈጣሪው አዞሮ እራሱን አዋርዶ ይሰግዳል። በእግዚአብሔር ፊት መቆምም ሆነ መስገድ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ የሰውነት መሥዋዕት ነው፡፡
*  ይህ ሥርዓተ ቅዳሴ (የጸሎት ክፍለ ጊዜ ) በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል፦
1. የዝግጅት ክፍል
2. የንባብና የትምህርት ክፍል
3. ፍሬ ቅዳሴያት ናቸው።
* ፍሬ ቅዳሴያት ብዛታቸው14 ነው።
እነሱም፦
1. ቅዳሴ ዘሐዋርያት
2. ቅዳሴ እግዚእ
3. ቅዳሴ ማርያም
4. ቅዳሴ ዘዮሐንስ ወልደ ነጓድጓድ
5. ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምዕት
6. ቅዳሴ ዘአትናቴዎስ
7. ቅዳሴ ባስልዮስ
8. ቅዳሴ ጎርጎርዮስ
9. ጎርጎርዮስ ካልእ
10. ቅዳሴ ዘኤጲፋንዮስ
11. ቅዳሴ ዘዮሐንስ አፈወርቅ
12. ቅዳሴ ዘቄርሎስ
13. ቅዳሴ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ
14. ቅዳሴ ዘዲዮስቆሮስ በመባል ይታወቃሉ።
+  እነዚህ ፍሬ ቅዳሴያት እንደ የበዓላቱ ይለዋወጣሉ።
++ የጌታችን በዓል ከሆነ … (ቅዳሴ እግዚእ)
+++ የጌታችን ምጽአት፣ ጳጉሜ እሑድ ቀን ከዋለች ሰንበት … (ቅዳሴ አትናቴዎስ)
++++ የእመቤታችን በዓል ከሆነ ቅዳሴ ማርያም … (ጎሳ ልብየ ቃለ ሰናየ)
የመላእክትና የሐዋርያት በዓል ከሆነ … (ቅዳሴ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ)
+++++ ከዘመነ ልደት እስከ ዘመነ ግዝረት … (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ካልዕ)
* በሥርዓተ ቅዳሴ ጊዜ የሚያገለግሉት ካህናት(ሉዑካን) 5 ናቸው።
- እነዚህም የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከዚያም በሚያንስም ሆነ በሚበዛ ሰው ቅዳሴን መቀደስ ይቻላል።
ለምሳሌ፦
+ 7 ከሆኑ በሰባቱ ምሥጢራተ  ቤተክርስቲያን ይመስላሉ።
++ 13(12)  በሐዋርያት እና በጌታችን  ምሳሌ በመሆን ይቀድሳሉ፤
+++ 24 በሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ። ይህ የሚሆነው እንደ ካህናቱ (አገልጋዮቹ) ብዛት ነው።
++++  ነገር ግን ካህን ከጠፋ ደግሞ አንድ ቄስና አንድ ዲያቆን በመሆን መቀደስ ይችላል። ሁለት መሆናቸው የመለኮትና የትስብዕት (የሥጋ) ምሳሌ ሆነው ይቀድሳሉ።
+++++ ሦስት ከሆኑ በሦስቱ ሥላሴ፣ አራት ከሆኑ በ4ቱ ወንጌላውያን ይመሰላሉ። - - ከሁለት ባነሰ ግን 1 ሆኖ ግን ቅዳሴ አይቀደስም፤ ቀኖናው የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት ይከለክላል፡፡
“ጸልዩ”
- ይህ የቅዳሴው የጸሎት ዓይነት ሲሆን ለ13 ጊዜያት ይባላል፡፡
- በሦስተኛው ክፍለ ቅዳሴ 4 ጊዜ ይባላል።
- ጸልዩን ዲያቆኑ ሲያውጅ ፊቱን ወደ ሕዝቡ ይመልስና እንዲጸልዩ ያውጃል፡፡ በዚህ ጊዜ ተሰጥዖ ካለ ተሰጥዖ ይመለሳል ከሌለ ግን “አቡነ ዘበሰማያት” ሕዝቡ እንዲደግሙ ያውጃል፡፡
ለምሳሌ፡-
+ ንፍቁ ዲያቆን “ጸልዩ በእንተ እለያበዕኡ መባዕ … መባን ስለሚያገቡ ሰዎች ጸልዩ” ሲል በዚህ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያት አይደገምም። ምክንያቱም የራሱ ተሰጥዖ ስላለው “ተወከፍ መባዖሙ ለአሃው ወተወከፍ መባዖን…” ይህ አቡነ ዘበሰማያት የሚተካ ጸሎት ነው፡፡
++ ድርገት ሲወርዱ “ጸልዩ በእንቲአነ” በሚባልበት ጊዜ እንድንጸልየው የሚያዘው የዳዊትን መዝሙር 150ኛውን መዝሙር ነው፡፡ ጸልዩ ብሎ ያዘዘው በዚህ ክፍል ያለ የዳዊትን 150ኛውን የመዝሙር ክፍል ነው ማለት ነው፡፡
*  እኛ ክርስቲያኖች ቅዳሴን ባስቀደስን ቁጥር፦
1ኛ፡ የኃጢአት ሥርየት ይገኛል፤ ምክንያቱም በአንቃዕዶ ሕሊና ይቅርታን ስለሚጠይቅ፣
2ኛ፡ በነፍስም በስጋም በረከትን ያገኛል፣
3ኛ፡ ጸሎቱም ይደመጣል፣
4ኛ፡ የመላእክትን በረከት በቀጥታ እንሳተፋልን ቅዳሴን አስቀድሶ ሥጋ ወደሙ ሲቀበል የዘለዓለምን በረከት ያገኛል፡፡
*  በተጨማሪም ቅዳሴ በማስቀደስ 4 ነገሮች ይገኛሉ እነዚህም፡-
1. ትምህርት
የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማ እና የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ትምህርት በቅዳሴ ጊዜ ያገኛል፡፡ ለምሳሌ የማርያምን ቅዳሴ (አባ ሕርያቆስ የደረሰውን) ቅዳሴ ሲቀደስ በውስጡ ምሥጢረ ሥላሴ፣ እና ምሥጢረ ሥጋዌ እንዲሁም ነገረ ማርያምን አምልቶ ይነግራል፡፡
2. ታሪክ
14ቱንም ቅዳሴ የሚያስቀድስ ሰው የቤተክርስቲያንን ታሪክ በቅዳሴ ውስጥ እንማራለን፡፡
3. ምክር
በቅዳሴ ውስጥ ተፋቀሩ፣ መጽውቱ፣ ተስማሙ፣ ጹሙ፣ ጸልዩ እየተባለ በቅዳሴ ውስጥ ሰፋ ባለ መልኩ ምክር ይሰጣል። ስለዚህ ቅዳሴን በማስቀደስ ምክርን ማግኝት ይቻላል ማለት ነው፡፡
4. ተግሣጽ
-  ቅዳሴ ውስጡ ተግሣጽን ይዞ እናገኝዋለን። ለምሳሌ በቅዳሴ እግዚእ ላይ ከወንድሙ ጋር የተጣለ ቢኖር ይተውለት ይላል። በዚህ የቅዳሴ ክፍል ውስጥ ራሳችንን ምን ላይ እንደቆምን ከሰዎች ጋር ያለንን ኅብረት ስምምነት ለፈጣሪ ራሳችንን ማስገዛታችንን እየገሠፀ ይነግረናል፡፡ እነዚህን መሠረታዊ የሆኑትን ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ቅዳሴ በማስቀደስ እናገኛቸዋለን፡፡
-  ቅዳሴ ንባብም ዜማም የሚቀርብበት የጸሎት ክፍል ነው፡፡ ሁላችንም የምንሳተፍበት ቄሴም ዲያቆኑም ምእመኑም የሚሳተፉበት ነው፡፡ “ኢትቁም እራቀከ ቅድመ ነቢየ እግዚአብሔር … በእግዚአብሔር ነቢይ ፊት ራቁትህን አትቁም” ይህ ማለት በቅዳሴ ጊዜ ሰው ካለመባ፣ ካለእጅ መንሻ በእግዚአብሔር ፊት ሳይዙ መቆም እንደሌለበት ያጠይቃል፡፡ ምንም ባይኖረን እንኳን ያለንን አነሰ ብለን ሳንሳቀቅ ደግሞም ሳንንቃት ይዘን በፊቱ መቅረብ አለብን። ከቻልን እጣኑን፣ ዘቢቡን፣ ጧፉን ሌላም ሌላም ይዘን መሄድ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ካህኑ በቅዳሴው መሃል ምዕናን ስለሚያስገቡት መባ የሚፀልየው ጸሎት አለ ምዕመኑም መባን ይዞ የማይመጣ ከሆነ ይህ ጸሎት ለማን ነው? ብሎ መጠየቅም ይገባል፡፡
ስለዚህ ቅዳሴን የምናስቀድሰው አስቀድመን ተዘጋጅተንበት መሆን አለበት፡፡ ለሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ጊዜ ባይኖረን ለቅዳሴ ግን ጊዜ መድበንለት ልናስቀድስ ይገባል፡፡
*  ቅዳሴ ለማስቀደስ ወደ ቤተክርስቲያን ስንመጣ ራሳችን፦
1ኛ: ቆምን ለማስቀደስ
2ኛ: የሚነበቡትን መጻሕፍቶች ከሕይወታችን ጋር እያዛመድን ለማዳመጥ ለመስራት
3ኛ: ቅዱስ ቁርባን ለመውሰድ የዘለዓለም ሕይወትንም ለማግኝት አምኖ መምጣት አለበት። በቅዳሴው የመግቢያ ክፍል ይህንኑ በዜማ “እስመጨረሻው ቅዳሴውን ያላስቀደስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ሲነበቡ ቆሞ ያላዳመጠ በመጨረሻም ቅዱስ ቁርባን ያልተቀበለ ከቤተክርስቲያን ኅብረት ልጅነት ይሰደድ” ይላል። ስለዚህ ራሱን አዘጋጅቶ መምጣት ይገባል፡፡
በተጨማሪም ሰው ለቅዳሴ ሲቆም 5ቱን የስሜት ሕዋሳቶቹን ሰብስቦ ወደ ቅዳሴው ትኩረት ሰጥቶ በንቃት ለቅዳሴ መቆም አለበት። ለዚህም ዲያቆኑ በመሃል በመሃል “ለጸሎት ተነሱ” እያለ ያውጃል ምዕመኑም ራሱን በእግዚአብሔር ፊት አዋርዶ ይቅርታን በመጠየቅ “አቤቱ ይቅር በለን” ይላል፡፡ አምስቱ የስሜት ሕዋሳት የሚባሉት አይን፣ ጆሮ፣ አፍንጫ፣ እጅ እና ምላስ በአንድት በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ያስቀድሳሉ
ለምሳሌ፡-
ዓይን፡-
ካህኑ ቅዳሴን ሲቀድስ በመንበሩ አጠገብ ቆሞ ብቻ አይደለም። የተለያዩ ዓይነት እንቅስቃሴዎች አሉ። እነዛን እንቅስሴዎች ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ መንፈሳዊ ምሥጢራዊ ትርጓሜዎች አሉዋቸው። እነዚህን እንቅስቃሴዎች ዓይን ያያል። ስለዚህ ዓይን ያስቀድሳል ማለት ነው፡፡
ጆሮ፡-
ካህኑም ዲያቆኑም ምእመኑም በአንድነትም ሆነ በተናጠል የሚያዜሙትን ዜማ፣ የሚያነቡትን ንባብ ይሰማል በዚህ ጊዜ ጆሮአችን ያስቀድሳል ማለት ነው፡፡
አፍንጫ፡-
የዕጣኑን መዓዛ በማሽተት አፍንጫችን ያስቀድሳል።
ምላስ፡-
ቅዱስ ቁርባን በመውሰድ፣ የቅዳሴውን ጸበል በመጠጣት በዚህ ጊዜ የመቅመስ ስሜታችን ያስቀድሳል፡፡
የመዳሰስ፡-
የመዳሰስ ስቀሜታችንም ስግዱ በተባለ ጊዜ፣ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ወንጌሉን ሲስም በመጨረሻም ሰዓት የካህኑን እጅ ለመባረክ ስንስም የመዳሰስ ስሜታችን ያስቀድሳል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ አምስቱም የስሜት ሕዋሶቻችን በተሟላ መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት መንገድ ምንድን ነው ቢባል ቅዳሴ ነው። በቅዳሴ ውስጥ የምናገኘው ትምህርት በአውደምህረት በኮርስ ከምናገኝው ትምህርት የተለየ ነው። ይኽውም በዜማ የታሸ ብዙ ሊቃውንት የደከሙበት መንፈስ ቅዱስ እንደገለፀላቸው ለሰው በቀላሉ የሚገቡ ትምህርቶች ናቸው። ሌላው ደግሞ ወንጌል ይነበባል፤ መልዕክታት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ከዓለም አቀፍ ከሆኑ ሁሉ እና በዜማ ስለሆነ ነው እንጂ (ምስባክ) የምንለው ከመዝሙረ ዳዊትም ውስጥ ይነበባል።
ስለዚህ 1 ሰው ቅዳሴን ሲያስቀድስ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን ከብሉይ እስከ ሐዲስ ድረስ ይማራል ማለት ነው። ረጅም ዘመን ያስቀደሰ በሕይወቱ ውስጥ ምሁር ማለት እርሱ ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንዳልነው ነው፡፡ የመላእክትን ሕይወት በምድር ላይ መኖር ማለት ነው፡፡
በቤተክርስቲያናችን ትልቁ ሱታፊ ቅዳሴን ማስቀደስ ነው። ይህንንም ከራስ አልፎ ወገኖቻችን ይህን ምሥጢር እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል። ልጆቻችን ከቅዳሴው እንዲሳተፉ ተሰጥዖ እንዲመልሱ፣ መባን ይዘው እንዲመጡ፣ ቅዳሴ ለማስቀደስ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ ቅዱስ ቁርባን እንዲቀበሉ ማድረግ ተገቢ ነው። ያለበለዚያ የሚሰጠውን የምናጣበት ደረጃ ላይ እንዳንደርስ የቀደመውን ሥርዓተ አምልኮ የሚፈፀምበት ሥርዓት እንዳይጠፋ የሚረከበን እንዳናጣ የቀደመው ለተተኪው ትውልድ ማስረከብ መቻል አለበት። ሰማያዊ ምሥጢር በምድረ ከተሠራባት ከመላእክት ጋር አንድ ሆነን ፈጣሪን ከምናመሰግንባት ከቅድስት ቤተክርስቲያን ሳያናውጥ ያኑረን አሜን፡
ወ ስ ብ ሐ ት   ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር !!
ወ ለ ወ ላ ዲ ቱ   ድ ን ግ ል !!
ወ ለ መ ስ ቀ ሉ   ክ ቡ ር ! 

Bitte besuchen Sie diese Seite bald wieder. Vielen Dank für ihr Interesse!