Äthiopisch Orthodoxe Tewahedo Debre Bistrat St. Gabriel Kirchengemeinde München e.V.

በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሀዶ ቤተክርስትያን፣የሙኒክ ደብረ  ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን 

ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን የሚዩኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን(ደብር) አመሰራረት እና ታሪክ።


 



















ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ እና ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳስት ፓትራያርክ ዘኢትዮጵያ።














ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ዲዮናስዮስ የጀርመን እና የአካባቢው አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ።














የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናው።




የሙንሽን ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን።

ክፍል አንድ። የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን አመስራረት እና የገጠማት ተግዳሮት። 

የሳባ ንግስት ለንጉስ ሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቶ ብዛት ከዚያ ወድያ አልመጣም ነበር።

ከኦፊርም ወርቅ ያመጣች የኪራም መርከብ እጅግ ብዙ የተጠረበ እንጨትና የከበረ ዕንቁ አመጣች።ንጉሡም ከተጠረበው እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት መከታ ፥ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤እስከ ዛሬም ድረስ በምድር ላይ እንደዚያ ያለ የተጠረበ እንጨት ከቶ አልመጣም፤በየትም ቦታ አልታየም።

(መጽሃፈ ነገሥት ቀዳማዊ ምእራፍ 10 ከቁጥር 10 -12) የሳባ ንግስት (የኢትዮጵያ ንግስት)

ባህር አቋርጣ፣ ረዥም መንገድ ተጉዛ የሰማችውን የሰለሞን መጠበብ በአይኗ ለማየት በቅታለች።ንግስቲቱ የንጉሥ ሰሎሞንን መጠበብ ለማየት ስትሄድ በአጋጣሚ ወይም እግረ መንገዷን ያደረገችው ጉዞ አልነበረም።ንጉሡ ሰሎሞን ጥበቡን ጥበብ ከሆነው ፈጣሪው እንዳገኘው ጠንቅቃ ታውቅ ነበር።ለዚህ ነው የሰሎሞንን መጠበብ እንዳየች ሰሎሞንን ስታመሰግነው ለሰሎሞን ጥበቡን የሰጠውን እግዚአብሔርን ጭምር ያመሰገነችው።ምክንያቱም ጥበብ ማለት እግዚአብሔር መሆኑን የሳባ ንግስት ጠንቅቃ ተረድታለች።ፈጣሪም ወደ ሶሎሞን ይዛቸው በሄደችው ገጸ በረከታት ስለተደሰተ ይመስላል ከተጠረቡ የእንጨት ስጦታዎች መካከል ለእግዚአብሔር ቤት መከታ እና እርሱን በዝማሬ ለሚያመሰግኑት መዘምራን መሰንቆ እና በገና መስርያ እንዲሆን የፈቀደው።ጌታ እየሱስም በፍርድ ቀን በዚህ ትውልድ ላይ ትፈርዳለች ጥበብን ፍለጋ ከሩቅ አገር መጥታለች እና ይላል።ይህ የክርስቶስ ምስክርነት ጥበብን ፍለጋ ሲል ጥበብ እግዚአብሔር ጠበብትን እንዴት ጥበበኛ እንደሚያደርግ ልትረዳ የፈጣሪን ጥበብ ለማየት እንደመጣች የሚያጠይቅ ነው።ክርስቶስ ጥበብን ልታይ አለ እንጂ ጥበበኛውን ልታይ አላለም።ጥበብን ካለ ጥበብ እራሱ እግዚአብሔር ሆኖ እናገኘዋለን።ጥንት በዘመነ ብሉይ አባቶቻችን ኢየሩሳሌምን ለመሳለም አገር አቋርጠው ይጓዙ እንደ ነበር፣በደረሱበት በጉዟቸውም ላይ ቅዱሳት መጻህትፍን ያነቡ እንደ ነበር፣ ቅዱሳት መጻሃፍትን በማንበባቸው ጥቅም አግኝተው በፈጣሪ ትእዛዝ ሐዋርያት በዳመና ተጭነው መጥተው ሀብተወልድ እና ስመ ክርስትና እንደሰጧቸው በሐዋርያት ስራ ምእራፍ ስምንት ላይ ታሪኩ ተጽፎ ይገኛል።ጥበብን ፍለጋ የሳባ ንግስት(የኢትዮጵያ ንግስት) ወደ ጠቢቡ ሰለሞን እንደ መጣች ሁሉ ሰብአ ሰገል (ጠበብት)ለሕጻኑ ለክርስቶስ ሊሰግዱ ከሩቅ አገር በኮከብ ተመርተው እንደመጡ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን ከእነዚህ ጥበበኞች መካከል አንደኛው ኢትዮጵያዊ ለመሆኑ በአብዛኛው የአለም የክርስትና እምነት ሊቃውንቶች የሚስማሙ ሲሆን በኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት እና በአንዳንድ አውሮፓዊ ሊቃውንትም ጭምር በኮከብ ተመርተው ለሕጻኑ ክርስቶስ ሊሰግዱ የመጡት ሦስቱም ጠበብት ኢትዮጵያዊያን እንደ ሆኑ ያምናሉ።እንደኛውም ይሁን ሦስቱም ከታሪኩ ምስክርነት የምንረዳው ኢትዮጵያዊያን ፈጣርያቸው እግዚአብሔርን ለማመስገን ምን ያህል የታመኑ እንደሆነ ነው።ልበ አምላክ ነብየ እግዚእብሔር ዳዊት በመዝሙሩ ማን ጌታ ፊት ቀርቦ እንደሚሰግድ እና የእጅ መንሻ እንደሚያቀርብ ከክርስቶስ ልደት በፊት በትንቢቱ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር።" በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ።የቴርሴስና የደሴቶች ስጦታን ያመጣሉ።የአረብ እና የሳባ ነገስታት እጅ መንሻ ያቀርባሉ።" (መዝ 72 ከቁ 9-11) ነብዩ ኢሳያስም "የግመሎች ብዛት፥የምድያምና የጌፌር ግመሎች ይሸፍኑሻል።ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ።ወርቅን እና እጣንን ያመጣሉ።የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ።" (ኢሳያስ 60) ሳባን እና አረብን አንድ አድርገው ዛሬ ላይ ታሪክን ለማዛባት ለሚሹ ነብዩ ከላይ በተጠቀሰው ትንቢቱ " የአረብ እና የሳባ ነገስታት!"በማለት ልዩነታቸውን ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል።ኢትዮጵያውያን በቅዱስ መጽሃፍ ውስጥ በተለያየ ስፍራ ለፈጣርያቸው ለእግዚአብሔር ምን ያህል ክብር እንደሚሰጡ እና ፈጣርያቸውን እንደሚወዱ ይህንንም በማድረጋቸው በረከትን ከፈጣርያቸው ያገኙ እንደ ነበር እውነተኛው ታሪክ ያስተምረናል።ዛሬም የእነርሱ የልጅ ልጆች የተመሰከረላቸው ቅዱሳን አባቶቻችን እና እናቶቻችንን ፈለግ በመከተል በየደረስንበት የተመቻቸ ሕንጻ ቤተክርስትያን የማግኘት እድል ባይኖረንም በጽዋ ማህበርም ቢሆን በመሰባሰብ ከፈጣርያችን ጋር ያለንን የምስጋና ግንኙነት እንዳይቋረጥ በምናደርገው ጥረት የሙንሽን ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ከመቆርቆሩ እና የመቆርቆሩም ውጥን ከመታሰቡ በፊት በሙኒክ ከተማ ስደተኞች በአንድነት እሚኖሩበት ታልኪርሸን በሚባል ስፍራ የስደተኞች መኖርያ ውስጥ ዛሬ በሚዪኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ውስጥ በአንጋፋነቱ የሚታወቀው የኪዳነ ምሕረት የጽዋ ማሕበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተካታይ በሆኑ ምእመናን እና ምእመናት የተመሰረተው። በጎቹ ያለ እረኛ ተበትነው እንዳይቀሩ የሚገደው አምላካችን እግዚአብሔር በሚዩኒክ ከተማ እና በአካባቢው የሚኖሩ ምእመናን እና ምእመናትን  ለማሰባሰብ እና ከእርሱ ጋር እየተገናኙ በስደት በሚኖሩበት አገር መጽናናት ይሆንላቸው ዘንድ የቸርነቱን ሥራ ከማከናወን ወደ ኋላ አላለም።

ለረዥም ጊዜ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አማካኝነት አገልጋይ ካህናት አግኝቶ ቤተክርስትያንን በቀሩት የጀርመን ግዛቶች ለመቆርቆር የሚደረገው ጥረት ከሞላ ጎደል ይሳካ ዘንድ የመልአከ ብርሃን ቀሲስ መስፍን ፈለቀ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ግንቦት 17 ቀን 1991(፩፱፻፰፫) ዓ.ም ከኢያሩሳሌም ወደ ጀርመን መምጣት ትልቅ ፈር ቀዳጅ ሁኔታን ፈጠረ።ካህኑ ለአጭር ግዜ በኮለኝ ቩፐርታል ከቆዩ በኋላ በቫደን ቩተንበርግ ዲያኮኒሽ ቬርክ ሰብሳቢነት ከሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን የሚዩኒክ እና ፍራይዚንግ መንበረ ሊቀ ጵጵስና ዶም ፕሬላት ዶክተር ቫልድ ሙለር፣ከሮተንበርግ ሽቱትጋርት ሀገረ ስብከት ዶክተር ቮልፍጋንግ ሮደል የፕሬላት ባወር የግል ረዳት ተወካይ፣ከጀርመን ሉተራን ወንጌላዊት ቤተ ክርስትያን ዲያኮኒሸስ ቬርክ ኪርሸን ራት ሐንስ ጆርጅ ፣ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ ከጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን እና በወቅቱ ለጀርመን አገር እንግዳ የነበሩት መልአከ ብርሃን ቀሲስ መስፍን ገብረ ማርያም ፈለቀ ሆነው የመጀመርያውን ውይይት አኪያሂደው ለሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል መመስረት ፈር ቀዳጅ የሆነ ስምምነት ላይ ደረሱ።በደቡብ ጀርመን ግዛት ውስጥ በሚገኙ ታላላቅ ከተሞች በሃይድልበርግ፣በሚዩኒክ እና በሽቱትጋርት በስምምነቱ መሰረት እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ  በቀሲስ መስፈን ገብረ ማርያም አማካኝነት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ ተወሰነ።ይህን ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን በማመቻቸት ረገድ አስፈላጊውን በጀት፣የካሕኑን እና የቤተሰቦቻቸውን መኖርያ፣ለስራቸው መቀላጠፍ ይረዳቸው ዘንድ የጀርመንኛ ቋንቋ ትምህርት የሚያገኙበትን ወጪ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከጥር ወር 1992 ዓ.ም ጀምሮ በፈጣሪ እርዳታ እና ፈቃድ የሚዩኒክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ለመሸፈን ፍላጎት  በማሳየቷ ሁኔታዎች በሰመረ መንገድ መጓዝ ቀጠሉ።ካህኑም ግዜ ሳያባክኑ የጀርመንኛ ቋንቋ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ጎን ለጎን ከሚዩኒክ ከተማ የስልክ ማውጪያ ደብተር ላይ የኢትዮጵያዊያንን የስልክ ቁጥር በመልቀም ስልክ ደውለው በመገናኘት የመጀመርያ ስብሰባ ለማድረግ ሙከራቸውን ቀጠሉ።ያድረጉት ጥረት ውጤት አግኝቶ በስልክ ከጋበዟቸው  መካከል አስራ አምስት የሚሆኑ ምእመናን እና ምእመናት ጥር ፲ ፩፱፻፹፬ (18.01.1992) ዓ.ም የከተራ እለት በአካል ከእርሳቸው ጋር ተገናኝተው ትውውቅ ያደረጉ እና በእለቱ የተከናወነውን የጸሎት መርሃ ግብር መካፈል የቻሉ ሲሆን ወደ ፊት ቤተ ክርስትያን መቆርቆር በሚቻልበት መንገድ ላይ ተስፋ ሰጪ ውይይት ለማድረግም በቅተዋል።በእለቱም ካህኑ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ማርች 01 1992 (የካቲት ፳፪ ፹፬) ዓ.ም ቅዳሴ እንዲኖር ጥሪ ለማቅረብ ማሰባቸውን በእለቱ ለተገኙት ምእመናን እና ምእመናት ገልጸው ሃሳቡ ተቀባይነት በማግኘቱ በተጠቀሰው ቀን ጥሪ ለሕዝቡ እንዲተላለፍ ተስማምተው ወሰኑ።


















እ.አ.አ በ02.02.92 ዓ.ም ለምእመናን እና ለምእመናት የተላለፈ የመጀመርያው የቅዳሴ መርሃ ግብር ጥሪ።

ወቅቱ በአገራችን የግዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ስላጣኑን በኢሕአዲግ የተነጠቀበት የሽግግር ግዜ ስለነበር እና ታላላቅ የቤተክርስትያን አባቶች ፓትርያርኩን ብፁእ አቡነ መርቆርዮስን ጨምሮ ከአገር የተሰደዱበት እና የብሔር ፖለቲካም የገነነበት  ወቅት ስለነበር የጥሪውን መንፈስ በጥርጣሬ የተመለከቱት ምእመናን እና ምእመናት መኖራቸው ግልጽ ነበር።ይሁን እና የተጠበቀውን ያህል ሰው ባይገኝም እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ 01 ማርች 1992 ዓ.ም ሊከናወን የታሰበው የቅዳሴ መርሃ ግብር ቫልድፍሪዶሆፍ በሚባል ስፍራ ለመጀመርያ ግዜ በፈጣሪ ፈቃድ በስኬት ሊከናወን ቻለ።

በተራ በየሰው ቤት ኪዳነ ምሕረትን ይዘክሩ የነበሩት በሙንሽን እድሜ ጠገብ የሆነው የኪዳነ ምሕረት ጽዋ ማሕበር አባላት የካህኑን መምጣት እንደተረዱ ባሉበት ሆነው ካህኑን ወደ እነርሱ እንዲመጡ በመጋበዝ ትምህርት እና ምክር ከቀሲስ መስፍን ያገኙ ሲሆን በእለቱ የጽዋ ማሕበሩ ወደ ክርስትያን ጉባኤው እንዲቀላቀል ካህኑ ያቀረቡትን ሃሳብ የጽዋ ማሕበሩ አባላት በመቀበላቸው ወደ ፊት ሊቋቋም የታሰበው ቤተክርስትያን አካል በመሆን ወደ ጉባኤው ተቀላቀሉ።ከዝያን ግዜ በኋላ የኪዳነ ምህረት ዝክር በየሰው ቤት በተራ መከናወኑ ቀርቶ በቤተክርስትያን መዘከር ተጀመረ።














በሙንሽን ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል አንጋፋ የሆነው የኪዳነ ምሕረት የጽዋ ማሕበር አባላት።

በዚህ መልክ ምእመናን እየተበራከቱ በመምጣታቸው ለዳግም ትንሣኤ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1992 ዓ.ም ለሁለተኛ ግዜ የቅዳሴ መርሃ ግብር ተከናወነ።

ከላይ በተዘረዘረው መልክ መንፈሳዊ አገልግሎቱ ተበታትነው የነበሩ ምእመናን እና ምእመናትን አሰባስቦ በጸሎት፣በስብከተ ወንጌል እና በዝማሬ ጉባኤው እየሰፋ ስለመጣ ምእመናን እና ምእመናት ደብሩ ስያሜ እንዲኖረው በስብሰባ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር ፴ ቀን ፩፱፹፭ ዓ.ም በመጠየቃቸው በእለቱ ለምርጫ ቀርበው ከነበሩት ከወላዲተ አምላክ ብጽኢት ድንግል ማርያም እና በመላኩ ቅዱስ ገብርኤል ስም ከተሰየሙት  ጽላት መካከል በመላኩ ቅዱስ ገብርኤል ስም የተሰየመውን ጽላት በመምረጥ በርካታ ምእመናን እና ምእመናት ድምጽ ሰጡ።የምርጫው ሁኔታ በዚህ መልክ ተጠናቆ  ቤተክርስትያኗን የማደራጀት ስራ ከተከናወነ በኋላ ሕዳር ፩፱ ቀን ፲፱፻፹፮ (28.11.93)ዓ.ም በብፁአን አባቶች በአቡነ ኤልያስ እና በአቡነ ዮሃንስ ቡራኬ የሙንሽን ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የሚል ስያሜ በኦፊሴል ቤተክርስትያኗ አገኘች።




 























የሮም ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የሚዩኒክ እና ፍራይዚንግ መንበረ ሊቀ ጵጵስና ፕሬላት ዶክተር ቫልድ ሙለር(እኚህ ሰው ለሚዩኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን መመስረት እና እዚህ ደረጃ መድረስ ከፍተኛ አስተዎጽኦ ያበረከቱ ሲሆኑ ከቤተክርስትያኗ ምስረታ ጀምሮ በተከበሩ የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በአላት ላይ ሳይለዩን አብረውን ያከብሩ ነበር።ዛሬ በጡረታ ቢገለሉም የቅዱስ ገብርኤልን አመታዊ በአል ብቅ እያሉ አብረውን ማክበራቸውን ያላቋረጡ ሲሆን እንደ እርሳቸው ያለ መልካም ሰው ዶክተር ሹፐን ተክተው ከእርሳቸው ጋር የነበረን አይነት መልካም ግንኙነት ሊቀጥል ችሏል!)





ዶክተር ፍሎሪያን ሹፐ።እኚህ ሰው ቤተክርስትያናችንን በማንኛውም መስክ በማገዝ የሚዩኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ምእመናን እና ምእመናት ባለውለታ ናቸው! እስከ ዛሬም መልካም ሃሳባቸው እና እርዳታቸው አልተለዩንም!ዶክተር ፍሎሪያን ሹፐ ከልብ እናመሰግናለን።



ዲያቆን ፍሬይ።ዛሬ የምንገለገልብትን ሕንጻ ቤተ ክርስትያን እንድናገኝ በመርዳት እና በኢቫንጀሊካል ቤተክርስትያን በኩል ክቤተክርስትያናችን የሚጠቅሙ ማንኛውንም ትብብር አቅማቸው የፈቀደው በማድረግ እስከ አሁን ከጎናችን ያሉ ሰው ናቸው። ከልብ እናመሰግናለን ዲያቆን ፍሬይ።

የተለያዩ የቤተክርስትያኗ ታሪክ ሰፍሮባቸው በሚገኙ ጽሁፎች ከላይ የተገለጹት የብጽእት ድንግል ወላዲተ አምላክ እና የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ስም ይዘው ያሉት ጽላቶች በትክክል መቼ እንደ መጡ ግልጽ የሆነ መረጃ ባይሰጡም ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ ምእመናን እና ምእመናትን በመጠየቅ የሚከተለውን መረጃ ለማግኘት ተችሏል።ከላይ በሰፈረው ታሪክ መሰረት ቤተክርስትያኗ በ28.11.93 እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ወይም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ሕዳር ፩፱ ቀን ፲፱፻፹፮ ዓ.ም ቅዱስ ገብርኤል የሚል ስያሜ ከማግኘቷ በፊት የቅዳሴ አገልግሎት ይፈጸም እንደ ነበር ይተርካል።ምንአልባት ይህ አተራረክ ከቤተ ክርስትያኗ ስያሜ በፊት ጽላት እንደ ነበረ ፍንጭ ይሰጣል።ጽላቶቹ የት እንደ ነበሩ መቼ እንደ መጡ ለማጣራት በተደረገው ሙከራ በትክክል የመጡበትን ቀን እና ዓ.ም የሚገልጽ ማስረጃ ባይገኝም ቤተክርስትያኗ ስያሜ ከማግኘቷ በፊት ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ጽላቶች በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ኤልያስ አማካኝነት ወደ ጀርመን አገር እንደ መጡ ለመረዳት ችለናል።ለዚሕም ነው ቤተክርስትያኗ የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የሚል ስሟን ከማግኘቷ በፊት የተከናወኑት በጣት የሚቆጠሩ የቅዳሴ ሥነ ስርአቶች ሊፈጸሙ የቻሉት።

ከቤተክርትያኗ ታሪክ እንደምንረዳው በወቅቱ ይህቺ አንጋፋ ደብር ከኮለኝ ቅዱስ ሚካኤል በመለጠቅ በጀርመን አገር የተመሰረተች፣ በሚዩኒክ  የምትገኝ ብቸኛዋ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን በመሆኗ፣ ወቅቱ የአለም ፖለቲካ መልኩን ቀይሮ ቀዝቃዛው ጦርነት ያበቃበት እና በአገራችን ውስጥ በተደረገ የመንግስት ለውጥ ምክንያት ቀደም ብለው ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ምስራቅ አውሮፓ ለትምህርት የመጡ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ትተው ወደ ምእራብ አውሮፓ ለመምጣት በመወሰናቸው፣ለከፍተኛ ትምህርት የመጡ ብቻ ሳይሆኑ በወቅቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የለቀቁበት እና በርካቶች በተለይ ወደ አገረ ጀርመን የጎረፉበት ዘመን ስለነበር፣ ኤርትራዊያን ወንድሞቻችን እንደ ዛሬ የእራሳቸው የሆነ ደብር ስላልነበራቸው በእነዚህና በመሳሰሉት ጉዳዮች የሚዩኒክን ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤልን ቤተክርስትያንን በፍጥነት ለማደራጀት ሁኔታዎች የተመቻቹ ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም። እርግጥ ነው በደቡብ ጀርመን ከሚዩኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ሌላ አብያተ ቤተክርስትያን አለመኖራቸው ለደብሩ አስተዳዳሪ የአገልግሎት ሁኔታውን ቀላል እንደማያደርግላችው እሙን ነው።በተለያዩ ስፍራዎች በመጓዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆችን በሰንበት ትምህርት ቤት እና በጽዋ ማሕበር በማደራጀት ስብከተ ወንጌል በመስጠት፣የመዝሙር ጥናት እንዲያደርጉ በማድረግ፣የጸሎት መርሃ ግብሮችን በማከናወን እና አልፎ አልፎም ስርአተ ቅዳሴ በመፈጸም መንፈሳዊ አገልግሎት ይከናወን ነበር።

ቤተ ክርስትያኗ አገልግሎቷን ለማጠናከር በአጥብያው ሰበካ ስር የተደራጁ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን በሚዩኒክ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን፣በኑረንበርግ የቅድስት ሥላሴን፣የኤርላንገንን፣በሽቱትጋርት የፍኖተወንጌል ቅድስት ማርያምን እና በካርልስሩሄ የአቡነ ተክለሃይማኖትን የሰንበት ትምህርት ቤቶች በማቋቋም ሁኔታዎች ሲፈቅዱ ካህኑ እቦታው በመገኘት በቅዳሴ እና በጸሎት መርሃ ግብር አገልግሎት ሲሰጡ ካህኑ በማይገኙበት ወቅት የእለተ ሰንበቱን አገልግሎት የጸሎት መርሃ ግብረን እና ስብከተ ወንጌሉን የሰንበት ትምህርት ቤቶቹ እራሳቸው ያከናውኑ ነበር።

በወቅቱ የነበረውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማጠናከር " ተምሮ ማስተማር!" በሚል መርሕ ተከታታይ በሽቱትጋርት፣በኑዩረንበርግ እና በተለይ በሚዩኒክ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1996 ዓ.ም ከአንድ ሳምንት በላይ የፈጀ ሴሚናር Blumen Strasse Mūnchen አካባቢ በሚገኘው Fraunkirche ውስጥ የተሰጠ ሲሆን ይህ ሴሚናር የቤተክርስትያን አገልጋዮችን እጥረት በመቀነስ ረገድ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አድርጓል።ቤተክርስትያኗ ያፈራቻቸውን አገልጋዮች በመጠቀም በአመት ሁለት ግዜ የቅዱስ ገብርኤልን አመታዊ በአል እና ትንሣኤን፣ኑዩረንበርግ ቅድስት ሥላሴ እራሱን ችሎ ደብር እስከ ሆነበት እለት ልደትን እና የቅድስት ሥላሴን አመታዊ በአል፣መስቀልን በሽቱትጋርት እና የጻዲቁ አባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አመታዊ በአላትን በካርልስሩሄ እያከበረች ምእመናን እና ምእመናት ከመናፍቃን ጠብቃ ዛሬ በደብር ደረጃ እራሳቸውን እንዲችሉ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች።ዛሬ በሚዩኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ጥላ ስር በርካታ የጽዋ ማሕበራት ቢኖሩም በአንጋፋነት የሚጠቀሱት አንጋፋው እና ከቤተክርስትያኗ መመስረት በፊት የተመሰረተው የኪዳነ ምሕረት የጽዋ ማሕበር፣የቅዱስ ገብርኤል የጽዋ ማሕበር፣ በኑይረንበርግ የቅድስት ሥላሴ የጽዋ ማሕበር፣ በሽቱትጋርት የቅድስት ማርያም የጽዋ ማሕበር እና በካርልስሩሄ የጻድቁ አባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት የጽዋ ማሕበር ሲሆኑ በአንጋፋነቱ በደብሩ ውስጥ የሚታወቀው የኪዳነ ምሕረት የጽዋ ማሕበር የተመሰረተው ከቤተክርስትያኗ ውጪ ቀደም ብሎ በተወሰኑ ወጣት ኦርቶዶክሳዊያን ነበር።

ይሁን እና የሚዩኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ከተመሰረተች በኋላ በስደተኞች መጠለያ እና በየመኖርያ ቤቱ ውስጥ ያደርጉ የነበረው ዝክር በማቆም በደብሩ አስተዳዳሪ የተደረገላቸውን ጥሪ በመቀበል በአገራችን የዘመን አቆጣጠር ከ፲፱፻፹፬ ዓ.ም ጀምሮ በቤተ ክርስትያኗ የመሰብሰብያ አዳራሽ ውስጥ ዝክሩን ማከናውን ጀመሩ።ከላይ የተጠቀሱት የጽዋ ማሕበራት ከዝክር ውጪ በአገራችን በኢትዮጵያ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቻችን ሰብአዊ እርዳታ በመለገስ ከፍተኛ አስተዋጽኦም በማድረግ ይታወቃሉ።

ቤተክርስትያኗ በጽዋ ማሕበር ምእመናን እና ምእመናትን አሰባስባ መንፈሳዊ መቀራረብን ከመፍጠር በተጨማሪ ምእመናን እና ምእመናት የሌሎች ደብራትን አመታዊ የንግሥ በአል እንዲያከብሩ የተሳላሚዎችን ጉዞ በማዘጋጀት ወደ ኮለኝ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን እና የፍራንክፈርት ቅድስት ማርያም የንግስ በአል ተሳታፊዎች ሆነው የበረከት ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ታመቻች ነበር።

በሞት የተለዩ ምእመናን እና ምእመናት አስከሬን ወደ ትውልድ አገራቸው ሄዶ እንዲያርፍ ከምእመናን እና ምእመናት የገንዘብ መዋጮ በመጠየቅ አስከሬናቸው በመላክ  የፈጸመችው ተግባር የማይዘነጋ ሲሆን ይህን አስከሬን ወደ ትውልድ አገር የመላክ ወጪ ችግርን ለማስውገድ መረዳጃ እድር እንደሚያስፈልግ ለምእመናን እና ለምእመናት ሃሳብ በማቅረብ ዛሬ በሚዩኒክ ከተማ ሁለት መረዳጃ እድራት እንዲቋቋሙ የደብሩ አስተዳዳሪ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው በአንድ የቤተክርስትያኗን ታሪክ በሚገልጽ መጽሄት ላይ ሰፍሮ ይገኛል።














 የኪዳነ ምሕረት የጽዋ ማበር።








 








የቅዱስ ገብርኤል የጽዋ ማሕበር።

 














ካርልስሩሄ የነበረው የፃድቁ አባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የጽዋ ማሕበር።

የሚዩኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን በስሯ በርከት ያሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በደቡብ ጀርመን በሚገኙ ከተሞች በመመስረት መንፈሳዊ አገልግሎት በቤተክርስትያኗ አስተዳዳሪ አማካኝነት ይሰጥ እንደ ነበር ከላይ የተገለጸ ቢሆንም የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ትምህርት ቤት መቼ እንደ ተቋቋመ መግለጹ አስፈላጊ ስለሆነ ስለ ሰንበት ትምህርት ቤቱ አመሰራረት በተለያዩ የቤተክርስትያኗን ታሪክ በሚዘክሩ ጽሁፎች ላይ የተገኘውን እንደሚከተለው አስፍረንዋል።የሙንሽን ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ትምህርት ቤት የተመሰረተው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ፩፱፻፹፬ (1992) ሲሆን የሰንበት ትምህርት ቤቱን ለማቋቋም ያስፈልግ የነበረው የመሰብሰብያ አዳራሽ እና የቅዳሴ ሥርአት የሚከናወንበት ቤተ ክርስትያንን ችግር በማቃለል ረገድ የሚዩኒክ ሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ከፍተኛ ክርስትያናዊ ትብብሯን አሳይታ አንድ የመሰብሰብያ አዳራሽ በመስጠት እና በወር አንድ ግዜ የቅዳሴ ሥርአት የሚከናወንበት ቤተክርስትያን በመፍቀዷ በወቅቱ የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ የነበሩት ቀሲስ መስፍን ፈለቀ የሰንበት ትምህርት ቤቱን ሊመሰርቱ ችለዋል።መዝሙር ክፍሉ በበርካታ ቤተክርስትያናቸውን በሚወዱ ወጣቶች በፍጥነት የተጠናከረ ሲሆን የተለያዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የቤተክርስትያኗ ጉባኤ እንዲሰፋ ይህ ቀረው የማይባል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።የሰንበት ትምህርት ቤቱ የትምህርት ክፍል በማቋቋም ፣ቲያትር እና አጫጭር ድራማዎችን፣መንፈሳዊ ጽሁፎችን (ግጥሞችን ወዘተ) በማዘጋጀት በየክብረ በአላቱ መንፈሳዊ ትምህርቶችን በማቅረብ ለምእመናን እና ለምእመናት አመርቂ አገልግሎት ሰጥቷል።የሰንበት ትምህርት ቤቱ አካል የሆነው የመዝሙር ክፍሉ በማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ተሳታፊ በመሆን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጣእም ያላቸውን መዝሙራትን እና ወረቦችን አጥንቶ በተለይ አመታዊ ክብረ በአላት ከፍተኛ ድምቀት እንዲያገኙ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል።የመዝሙር ክፍሉ አዳዲስ መዝሙራትንም በካሴት በማስቀረጽ ለሽያጭ አቅርቦ ለቤተ ክርስትያኗ ገቢ ማስገኘትም ችሏል።










 











































የተለያዩ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ፎቶግራፎች።


















ሕጻናት መዘምራን በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ላይ መዝሙር ሲያቀርቡ።











ከሙንሽን ሮም ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ለመሰብሰብያ የሚሆን አዳራሽ እና የቅዳሴ መርሃ ግብር በሳምንት አንድ ቀን ለማከናወን በዜንዲሊንገርቶር በሚገኘው ----- ካቶሊክ ቤተክርስትያን ውስጥ ፈቃድ ከተገኘ በኋላ የሚቀጥለው ዋናው የቤተክርስትያኗ ተግባር የነበረው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ማስመረጥ ሲሆን የመጀመርያው የሙንሽን ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር በቤተክርስትያኑ አስተዳዳሪ እና ቀጥሎ ስማቸው በተዘረዘረው ምእመናን እና ምእመናት 

1ኛ/በቀሲስ መስፍን ፈለቀ(የቤ/ክ/አስተዳዳሪ)

2ኛ/በአቶ ብርሃኑ ወልደ ጻድቅ

3ኛ/በአቶ አስፋው ተስፋዬ

4ኛ/በአቶ ጌታቸው አበበ 

5ኛ/በወ/ሮ ጥሩዬ ተሰማ

6ኛ/በወ/ሮ ብዙነሽ 

እንደ እ/ኤ/አ ነሐሴ ወር 1994 ዓ.ም ተቋቋመ።

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳድሩ ተቋቁሞ በርካታ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የተደረጉ ሲሆን በዋናነት ከሚጠቀሰት ተግባራት አንዱ ቤተክርስትያኗ ያለባትን የአገልጋዮች ችግር ለማቃለል " ተምሮ ማስተማር!" በሚል መርህ ተዘጋጅቶ ለአንድ ሳምንት የተሰጠው ሴሚናር ነው።ይህ ሴሚናር ሙሉ በሙሉ የነበረውን የአገልጋዮች እጥረት ባያስወግደውም ችግሩን በመቀነስ ረገድ ያደረገው አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም።በዚህ ሴሚናር ላይ ትምህርት በመስጠት የተሳተፉት ዛሬ በሞት ከመኃከላችን የተለዩን ብጹእ አቡነ ዮሃንስ የአውሮፓ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ታቦተ ሕጉ በአውደ ምህረት ላይ ለገብርኤል በአለ ንግስ እንደ ቆመ ያስተላለፉት መመርያ እና ቃለ ምእዳን ለምእመናን ከፍተኛ መነቃቅያ ምክንያት ሆኖ የእራስ የሆነ ቤተክርስትያን የመስራት እቅድ ተጠነሰሰ።








ብጹእ አቡነ ዮሃንስ የአውሮፓ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቤተ ክርስትያን ስለ መስራት እ.ኤ.አ 1996ዓ.ም የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤልን በአል ለማክበር ለተሰበሰበው ሕዝበ ክርስትያን በወቅቱ ያስተላለፉት መልእክት። 

ይህን የሊቀ ጳጳሱን መመርያ ተግባራዊ ለማድረግ እና ከነበረው የተውሶ ቤተ ክርስትያን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ለመገላገል በደብሩ አስተዳዳሪ እና በሕዝበ ክርስትያኑ ላይ ይታይ የነበረው ፍላጎት ስለ አየለ ከላይ እንደ ጠቀሰው እ.ኢ.አ በሐምሌ ፩፱ ቀን ፩፱፻፹፰ (እ.ኤ.አ ሐምሌ ወር 1996ዓ.ም) የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ የንግስ በአል በተከበረበት እለት የተሰጠውን መመርያ እና ቃለ ምእዳን መሰረት በማድረግ በእለቱ የሙንሽን ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን በይፋ ስም ያገኘበትን ሦስተኛ አመት አስመልክቶ በሚደረገው በአል ቀን ምእመናን እና ምእመናት እንዲገኙ በመጋበዝ  እ.ኢ.እ በሕዳር ፩፱ ፩፱፻፰፱ ዓ.ም(እ.ኤ.አ ሕዳር 1996 ዓ.ም) በርካታ ምእመናን እና ምእመናት በተገኙበት የደብሩ አስተዳደሪ አጠቃላይ የቤተክርስትያኗን እንቅስቃሴ የሚመለከት ዘገባ አቀረቡ።ከዘገባው በኋላ በሙኒክ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስያን የባሕላዊ እና ማኅበራዊ ማእከል አሰሪ ኮሚቴ በመመስረት ረገድ ከፍተኛ ውይይት ተደርጎ ይህን ኮሚቴ ሊያስመርጥ የሚችል አንድ የአስመራጭ ኮሚቴ በቤተክርስትያኑ አስተዳዳሪ ሰብሳቢነት ተሰይሞ ይህ አስመራጭ ኮሚቴ በተጨማሪ  ኮሚቴው የሚመራበትን ደንብ አርቅቆ በወሩ ለታሕሣስ ገብርኤል ዋዜማ እንዲያቀርብ ተወሰነ።በውሳኔውም መሰረት የአስመራጭ ኮሚቴው የታህሳስ ገብርኤል ዋዜማ ያዘጋጀውን ደንብ ከተለያዩ ስፍራዎች የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤልን አመታዊ የንግስ በአል ለማክበር በተገኘው ሕዝበ ክርስትያን፣የደብሩ ምእመናን እና ምእመናት፣ በጀርመን የኢት/ኦር/ተ/ አብያተ ክርስትያናት አስተዳዳሪ የነበሩት ሊቀ ካህናት መርአዊ ተበጀ በተገኙበት በደንቡ ላይ ውይይት ተደርጎ ሰባት አባላት ያሉት የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን የባሕላዊ እና ማኅበራዊ ማእከል  አሰሪ ኮሚቴ ተቋቋመ።እ.ኤ.አ 01 ጥር 1997 ዓ.ም የመጀምርያ ስብሰባውንም አከናውኖ ቀጥሎ በተጠቀሰው ሁኔታ የስራ ክፍፍል በማድረግ ስራውን ጀመረ።

1/ቀሲስ መስፍን ገብረ ማርያም። ሰብሳቢ
2/አቶ ፍቃዱ ተስፋዬ።          ም/ሰብሳቢ
3/አቶ ከበደ ወ/ማርያም።      ገንዘብ ያዥ
4/አቶ ይሔይስ ታፈሰ።         ንብረት ክፍል
5/አቶ ካልዓዩ ጽጌ።     የእቅድ እና ቴክኒክ  ክፍል
6ኛ/አቶ ዮሃንስ ኤፍሬም።     ሂሳብ ሹም
7ኛ/ ዲያቆን በጋሻው ወ/ወልደ ሰንበት ጸሃፊ












በሚዩኒክ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን  የባሕላዊ እና ማሕበራዊ ማእከል አሰሪ ኮሚቴ አባላት ከብጱእ አቡነ ዮሃንስ ከአውሮፓ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጋር።











በሚዩኒክ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን የባሕላዊ እና ማሕበራዊ ማእከል አሰሪ ኮሚቴ አባላት በከፊል።

ይህ የባሕላዊ እና ማሕበራዊ ማእከል አሰሪ ኮሚቴ ከተቋቋመበት እለት ጀምሮ በርካታ ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን በተለይ ወደ ፊት ሊያሰራው ያቀደውን የሕንጻ ዲዛይን በወቅቱ የኑዩረንበርግ ከተማ ነዋሪ በሆኑት በአቶ ለማ ብርሃኔ አሰርቶ በማቅረብ ለማእከሉ ማሰርያ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ የተለያዩ ዘዴዎችን በመቀየስ ስራውን ቀጥሎ ገቢ ማስገኘት የቻለ ሲሆን በተለይ" የተስፋ ሰነድ!" የሚል ለቤተክርስትያን ማሰርያ የሚሆን ገቢ ምእመናን እና ምእመናት የወር ደሞዛቸውን በአመት የሚለግሱበትን ቅጽ አዘጋጅቶ በማስሞላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጎ በተቋቋመ በሁለት አመቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች 142,161.34 የጀርመን ማርክ መሰብሰብ ችሏል።










ለባሕላዊ እና ማሕበራዊ ማእከል ገቢ ማሰባሰብያ የተስፋ ሰነድ።







ሊሰራ ታቅዶ የነበረው የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን የባሕላዊና ማሕበራዊ ማእከል ሕንጻ ፕላን ከፊት ለፊት ሲታይ።











የባሕላዊ እና ማሕበራዊ ማእከል አሰሪ ኮሚቴ በተቋቋመ በሁለተኛው አመት ያቀረበው የገቢ ዘገባ።(ከአምስተኛ አመት መታሰብያ ልዩ እትም ላይ የተወሰደ።)

የመጀመርያዎቹ የቤተክርስትያኗ እንቅስቃሴዎች በተለያየ አቅጣጫ ስኬታማ እና በርካታ ምእመናን እና ምእመናትን ያሳተፉ ቢሆንም 
ትራንስፓረንት የሆነ አስራር የለም የሚሉ እና በወቅቱ እንቅስቃሴ ላይ በተለይ በፋይናንስ ጉዳይ ላይ የሚያጉረመርሙ ደፍሮ የሉም ለማለት አይቻልም።ይህ ግዜ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ ሆነው በአጠቃላይ የቤተክርስትያኗ የብርሃን ዘመን ነበር ማለት ይቻላል።በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ተሰርተዋል።በወቅቱ በርካታ ምእመናን እና ምእመናት ቤተክርስትያናቸውን ለመስራት የተስፋ ሰንድ የሚባለውን ቅጽ በመሙሏት የአመት ደሞዛቸውን መለገሳቸው በቤትክርስትያኗ መዝገብ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።ብዙ ምእመናን እና ምእመናት በቤተክርስትያናቸው ውስጥ በተክሊል እና በቁርባን ተጋብተዋል።በርካታ ሕጻናቶች ሐብተ ወልድ እና ስመ ክርስትና አግኝተውበታል።

የወላጅ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሕጽናት ስለ ሃይማኖታቸው እና ስለ ቤተክርስትያናቸው ትውፊት እንዲያውቁ ክፍተኛ ጥረት ተደርጎ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል።በመንፈሳዊ አገልግሎትም በኩል ቁጥራቸው የማይናቅ ዲያቆናት የዲቁና ማእረግ አግኝተው ቤተክርስትያኗን አገልግለዋል።አንድ ዲያቆንም የቅስና ማእረግ አግኝተው የደብሩ አስተዳዳሪን በመራዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማድረግ ችለዋል።እስከ አውሮፓውያኑ የአዲሱ ምእት አመት መጀመርያ ማለትም እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ አንዳንድ ተጨባጭ የሆኑ ማስረጃ ያልቀረበባቸው ጉምጉምታዎች እንዳሉ ሆነው ነገሮች በሙሉ በጥሩ ሁኔታ ሊራመዱ ችለው ነበር።ከአውሮፓዊያኑ ሜላንየም በኋላ ግን በቤተክርስትያኑ ምስረታ የመጀመርያ አመታት ብልጭ ብለው ታይተው የነበሩ ግልጽ አሰራሮች እየተዳከሙ መጥተው ምእመናን እና ምእመናት ለሁለተኛ ግዜ በተመረጠው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር እና በደብሩ አስተዳዳሪ ላይ አልመደሰታቸውን በግልጽ መናገር ጀመሩ።

ይሁን እና የመጀመሪያው የቤተ ክርስትያን አሰሪ ኮሚቴ ከተቋቋመ ከስምንት አመት በኋላ እ.ኤ.አ 2004 ዓ.ም የተመረጠው የቤተክርስትያን አሰሪ ኮሚቴ እና በዘጠኝ አባላት የተቋቋመው የበአል አዘጋጅ ኮሚቴ ለቤተክርስትያን ማሰርያ ገቢ ለማስገኘት ያደርገው የነበረው አስተዎጽኦ እጅግ የላቀ ነበር።የሳመር የጎዳና ላይ ፌስት በአመት አንዴ በማዘጋጀት፣በኢትዮጵያን አዲስ ዘመን ምክንያት የበአል ዝግጅት በማድረግ፣ምግብ እና መጠጥ ከቅዳሴ በኋላ በደብሩ አዳራሽ ውስጥ በመሸጥ፣በንግሥ እና በተለያዩ በአላት ላይ ንዋየ ቅድሳትን በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ በማስገባት መታተሩን ቀጠለ።



















በአመት አንዴ የሚከበረው የሽትራሴን ፌስት ይህን ይመስል ነበር።













የሚዩኒክ  ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን  የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በሳመር ፌስት ላይ  መዝሙር ሲያቀርቡ።

በወቅቱ ቤተክርስትያኗ እንደ ዛሬው በአመት ከ62,000 ዩሮ በላይ ለማውጣት የሚያስገድዳት የቤት ኪራይ እና የአገልጋይ ካሕን የደሞዝ የመሳሰሉት ወጪ ስላልነበረባት፣ ብቸኛዋ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን በመሆኗ ከተለያየ አቅጣጫ በተለይ ከሙዳየ ምጽዋት የሚገኘው፣በንግሥ በአል ላይ ጃንጥላ በማዞር የሚገኘው ገቢ የቤተክርስትያን ባለቤት በፍጥነት ሊያደርገን ይችላል ብለው በሚያስቡ ምእመናን እና ምእመናት በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ እና በአስተዳዳሪው መካከል ቀድሞ የነበረው መተማመን በከፊል መቀዛቀዙ እየተባባሰ መጥቶ ነበር።ወቅቱ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ የመጣበት ስለ ነበር በፊት ለፊት መነጋገር አንችልም ብለው ያሰቡ ምእመናን በተለያዩ ድረ ገጽ ላይ የቤተክርስትያኗን አጠቃላይ አስራር በመቃወም ጽሁፋቸውን ማስፈር ጀመሩ።የደብሩ አስተዳዳሪም  ለጽሁፎቹ መልስ ለመስጠት በአውደ ምሕረት ላይ ግዝያቸውን እና ጉልበታቸውን ይጨርሱ ጀመር።ነገሮች በዚህ መልክ እያሉ ነበር ለደብሩ አስተዳዳሪ እፎይታ ያመጣ እና እንደ ድል የተቆጠረ፣ሕዝበ ክርስትያኑን በደስታ ያስፈነጨ ነገር የተከሰተው።በደብሩ አስተዳዳሪ እና በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ የአሰራር ግልጽነት የማይስማሙ ምእመናን እና ምእመናትም ጭምር የደስታው ተካፋይ በመሆን ፈነደቁ። ሪዝ ሽትራሴ 100 ላይ የሚገኘው የኢቫንጄሊካል ቤተ ክርስትያን ስጦታ እንደ ቀረበልን ታወጀ!በተውሶ ቤተክርስትያን ለሚሰቃየው ሕዝበ ክርስትያን ይህ ዜና እንደ ገና እንደ መወለድ ነበር።ወሬው በሙሉ "ሁሉም ነገር ወደ ሪዝ ሽትራሴ!"ሆነ። ምእመናን እና ምእመናት እንደ ችሎታቸው መጠን በስጦታ ተገኘ የተባለውን ሕንጻ የውስጥ አካል ለእኛ ቤተክርስትያን በሚስማማ መልክ ለመስራት መረባረብ ጀመሩ።ዛሬ ላይ እርግጥኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም ውስጡን ለማስተካክል ከ 25 እስከ 32 ሺህ ዩሮ ወጪ ሳይደረግ እንዳልቀረ በወቅቱ ሳይነገር አልቀርም።የቤተክርስትያኑን ግርግዳ በቅዱሳት ስእል ለማስጌጥ፣ለአልባሳት፣ለወለል ምንጣፎች፣ለንዋየ ቅድሳት እና ለመሳሰሉት የወጡትን ውጪዎች ምእመናን ተረባርበው በመሸፈናቸው የቤተክርስትያኑን ውስጥ የማስጌጥ ስራ እና አዳራሹን ለአገልግሎት የማዘጋጀት ሥራ በአጭር ግዜ ተጠናቆ እ.ኢ.አ ታህሳሥ  ፪፼ (2000) ዓ.ም እ.ኤ.አ 29 ዲሴምበር 2007 ዓ.ም የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ የንግስ በአል እለት ሕንጻ ቤተ ክርስትያኑ በብፁእ አቡነ እንጦንስ በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከተለያዩ የጀርመን ግዛት በአሉን ለመሳተፍ በመጡ በርካታ ምእመናን እና ምእመናት፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ቤተ ክርስትያኑ ተባርኮ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።







ብፁእ አቡነ እንጦንስ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና በጀርመን አገር የሚገኙ አብያተ ክርስትያናት አስተዳዳሪዎች።


















ሪዝ ሽትራሴ የሚገኘው ቤተክርስትያን ተባርኮ ስራ ከመጀመሩ በፊት ዋዜማው ይህን በመሰለ ሁኔታ ተከብሮ ነበር።

ከላይ እንደተጠቀሰው በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ እና በደብሩ አስተዳዳሪ ላይ ከምእመናን እና ከምእመናት ይነሱ የነበሩ ጉምጉምታዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቀበሩ በሚመስል ሁኔታ ሁሉም ነገር ተዘንግቶ ምእመናን እና ምእመናት ቤተክርስትያንን ወደ ማስተካከሉ እና ወደ ማደራጀቱ ሥራ ስለ አተኮሩ ቤተክርስትያኑን ለመባረክ የተደረገው በአል እና ዋዜማው እጅግ የደመቀ ነበር።አገልግሎቶች ቤተክርስትያኗ ስተመሰረት በነበረው ሁኔታ ጥሩ እንቅስቃስያቸውን ቀጠሉ።የወላጅ ኮሚቴውም ከወትሮው ለይት ባለ ሁኔታ ተንቀሳቅሶ የሚሰራበት ሰፋ ያለ ቦታ በማግኘቱ ልጆችን በማስተማር እና በማነጽ ረገድ ይጫወት የነበረውን ሚና በሰፊው ቀጥሎ ተተኪ ሕጻናት ዘማሪዎችን መተካት የሚችልበት አይነት ሁኔታ ማሳየት ጀመረ።










ቤተ መቅደሱን ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ የእምነት ሥርአት መፈጸምያ በሚሆን መልኩ የመጀመርያው ሥራ ይህን በሚመስል መልክ ተዘጋጅቶ ነበር።
















ምእመናን ቤተ መቅደሱን በቅዱስ ስእላት በማስጌጥ ሥራ ላይ። ቤተ መቅደሱን በቅዱስ ስእላት ማስጌጡ ከተከናወነ በኋላ ይመስል ነበር።






























የቤተ ክርስትያኑን ውስጥ በቅዱሳት ስእል ለማስጌጥ፣ ወለሉን ምንጣፍ ለማልበስ እና ለነዋየ ቅድሳት መግዣ የሚሆነውን ወጪ የሸፈኑ ምእመናን እና ምእመናት ስም ዝርዝር። 

ይሁን እና በጋለ ሥሜት ይደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎች በድጋሚ በተለያዩ ምክንያቶች  እያሽቆለቆሉ መምጣት ጀመሩ።ቤተክርስትያኑ በስጦታ ተገኘ የሚለው መጀመርያ ላይ ለሕዝበ ክርስትያኑ የተሰጠው መረጃ ሕዝበ ክርስትያኑ ቀደም ብሎ ያደርግ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ በተለይ የሰበካ ጉባኤ አባልነት ክፍያ እንዳይከፍል ወደ ኋላ እንዲል ያደረገው ሲሆን በተጨማሪ የቤተክርስትያኗ ገንዘብ እየባከነ ነው የሚለው ጭምጭምታ እያየለ በመምጣቱ ብክነቱን ለማስተባበል በደብሩ አስተዳዳሪ የተመረጠው መንገድ የበለጠ ሕዝበ ክርስትያኑን እያሸሸው ስለመጣ ነገሮች በሚፈለገው መንገድ ወደ ነበሩበት በቀላሉ ሊመጡ አልቻሉም።በስተመጨረሻ በተደጋጋሚ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ምክትል ሊቀ መንበር በአቶ ብርሃኑ ገብረ መስቀል አማካኝነት በአውደ ምሕረት ላይ ቤተክርስትያኑን በስጦታ እንዳላገኘን ተክራይተን እንደ ሆነ እና ኪራይ ለመክፈልም ምእመናን እና ምእመናት የሰበካ ጉባኤ የአባልነት ክፍያ ወቅቱን ጠብቀው መክፈል እንዳለባቸው ያሳስብ ጀመር።ያመጣው ለውጥ ግን አልነበረም።የአስተዳዳሪውም ኃይለኝነት እየቀጠለ የሕዝበ ክርስትያኑም እምቢተኝነት እያየለ መጥቶ እሁድ ቅዳሴ  የሚሳተፉ ምእመናን ቁጥር አለቅጥ እያነሰ መምጣት ጀመረ።የቤተ ክርስትያኑንን ገንዘብ አስተዳዳሪው አባክነውታል የሚለው እስተሳሰብ እያየለ መጥቶ ባበጠበት ወቅት የደብሩ አስተዳዳሪ ቤተክርስትያኗን በጀርመን ሕግ መሰረት ፈራይን(ሬጂስተርድ አሶሴሽን) ሊያደርጉ ማሰባቸውን ለማብሰር ምእመናንን እና ምእመናትን በጠሩበት ስብሰባ ላይ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የነበረ የገንዘብ መባከን ጉዳይ ፊት ለፊት ተገልጦ ለመጀመርያ ግዜ በገንዘብ ጉዳይ የደብሩ አስተዳዳሪ ጥያቄ ቀረበላቸው።እንደ ሌላው ግዜ በቀላሉ የሚመክቱት አልነበረም።በዚህ ሁኔታ የጀመረው ማስረጃ ያልቀረበበት ክስ በማስረጃ እየተጠናከረ መጥቶ ጉዳዩ በመካከለኛው እና በምእራብ አውሮፓ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአቡነ እንጦንስ ጉዳዩ እንዲታይ ቀጠሮ ተያዘ።እ.ኤ.አ በ 2011 ዓ.ም መጀመርያ ላይ ብጹእ አቡነ እንጦንስ በተገኙበት ስብሰባ የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያንን የመሰረቱት እና ለዚህ ያበቋት  አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃን ቀሲስ መስፍን ፈለቀ መቶ ስልሳ አምስት ሺሕ ዩሮ (ወደ መቶ ሰማንያ አምስት ሺሕ ዶላር ገደማ) እንዳባከኑ በኦፊሴል አመኑ!ይህ ቀን በጀርመን እና በአውሮፓ በጥንካሬዋ ለምትታወቀው ደብር የጨለማ ግዜ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።መቶ ስልሳ አምስት ሺሕ ዩሮ አስተዳዳሪው አባክኘዋለሁ ብለው የእምነት ቃላቸውን የሰጡበት ቢሆንም የባከነው የቤተክርስትያኗ ገንዘብ ከዚያም በላይ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።ይህን እምነታቸውን ትክክል የሚያደርግ ማስረጃም ሲያቀርቡ ለሃያ አመታት የቤተክርስትያናችን ገቢ ጎድሏል በተባለው መጠን መወሰን በጣም የዋህነት እንደ ሆነ ያሳስቡና በአሁኑ ወቅት ቤተክርስትያናችን በአጭር ግዜ ውስጥ ሰብስባ በካዝናዋ ያላትን የገንዘብ አቅም እንደ ምሳሌ አድርገው ያቀርባሉ።ዛሬ ስድስት መቶ ሰላሳ ሦሶት ሺሕ ዩሮ በቤተ ክርስትያን ማሰርያ ካዝና ውስጥ ብቻ ይገኛል።ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ የተሰበሰበው በስድስት እና ሰባት አመት ውስጥ ነው።ሌላው መከራከርያ ሊሆን የሚችለው እውነታ ከአንድ አመት በፊት በ 2019 ዓ.ም የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ የቤት ኪራይ፣የካህን ደሞዝ ከፍሎ እና ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎችን ሸፍኖ የተረፈ ገቢውን መቶ ሺሕ ዩሮ ወደ ቤተክርስትያን ማሰርያ ካዝና እንዲገባ ያደረገ ሲሆን በሚቀጥለው አመት በ 2020 ዓ.ም በኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሺኝ ወቅት ደግሞ ሃምሳ ሺሕ ዩሮ ወደ ቤተ ክርስትያን ማሰርያ ካዝና ማስገባት ችሏል።በሁለት አመት የግዜ ክልል ለቤተክርስትያን ማሰርያ ከሚሰበሰብ ገንዘብ ውጪ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ከልዩ ልዩ ገቢዎች የተገኘውን ገንዘብ ለአስተዳደራዊ ስራው የሚያውለውን የሁለት አመት ወጪ ከመቶ ስድሳ ሺሕ ዩሮ በላይ የሚገመተውን ሸፍኖ  የተረፈውን መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር ወደ ቤተክርስትያን ማሰርያ ካዝና ማስገባት ከቻለ የቤት ኪራይ እና የካህን ደሞዝ በማይከፈልበት ሃያ የመልአከ ብርሃን ቀሲስ መስፍን ፈለቀ የአስተዳደር ዘመን ምን ያህል ገንዘብ ሊሰበሰብ እንደሚችል ለመገመት ቀላል ነው።

" በሁለት አመት ውስጥ ለአስተዳደራዊ ስራ የወጣውን ወደ መቶ ስልሳ ሺሕ ዩሮ ገደማ ሳይጨምር አሁን በስራ ላይ የሚገኘው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ  አስተዳደር ወደ ቤተ ክር ስትያን ማሰርያ ካዝና ያስገባው መቶ ሃምሳ ሺሕ ዩሮ እና መልአከ ብርሃን ቀሲስ መስፍን በሃያ አመት ሰብስበውት የነበረው ገንዝብ መቶ ስድሳ አምስት ሺሕ ዩሮ በመጠን እኩል ሊሆን አይችልም!"በማለት ከላይ ከተጠቀሰው መጠን በላይ በርካታ ቁጥሩን መግለጽ የማይቻል ገንዘብ መባከኑን ማስረጃ በማቅረብ መከራከርያውን ማጠናከር ይቻላል።

የሆነ ሆነና በወቅቱ የካህኑ ዘመድ ነን የሚሉ፣ አብረዋቸው ሲበሉ፣ሲጠጡ፣ሲያጅቧቸው የኖሩ፣ ያለ እኛ ቤተኛ የለም ሲሉ የነበሩ ምእመናን እና ምእመናት ከሌላው ምእመናን እና ምእመናት የከፋ የእርግማን ዶፍ  በቀሲስ መስፍን ፈለቀ ላይ ያወረዱባቸው ጀመር።

ገንዘቡ እየባከነ እንደ ነበር አስቀድሞ መረጃ ይኑራቸው አይኑራቸው የሚያውቀት እነ እርሱ እና ፈጣሪ ብቻ ነበር።አንዳንዶቹ በቂ መረጃ እንደነበራቸው ይታማሉ።ምናልባት እኮ እነኚህ የመልአከ ብርሃን ቀሲስ መስፍን ፈለቀ ወዳጆች እውነተኛ ወዳጃቸው ከነበሩ ይህ ሁሉ ጥፋት ሳይጀመር ከዚህ ማጥ ውስጥ ሊያወጧቸው የሚችሉበት  የተመቻቹ መስለው የሚታዩ ሁኔታዎች ነበሩ ቢባል ለእውነትነቱ ምንም ጥርጥር የለውም።

የመልአከ ብርሃን ቀሲስ መስፍን ጉዳይ በእርግማን ብቻ አላቆመም!የደብሩ አስተዳዳሪ  በሚዩኒክ አቃቤ ሕግ ተከሰው ፍርድ ቤቱ ባስዋለው ችሎት በሃያ አንድ ጥፋት ተከሰው ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ከሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ጋር የነበራቸው ግንኙነት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ ተቋረጥ።በሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ውስጥ ይደረጉ የነበሩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ቀዝቅዘው የቤተክርስትያኗ ሕልውና ጥያቄ ምልክት ውስጥ የገባበትም ሁኔታ ተፈጠረ።ያ ዘወትር እሁድ በቅዳሴ፣ስመ ክርስትና በሚቀበሉ ሕጻናት እና በቤተ ሰዎቻቸው፣ ጋብቻቸውን በቅድስት ቤተክርስትያን በሚፈጽሙ ምእመናን ሰርግ ዝማሬ ደምቆ ይታይ የነበረው ደብር ባዶ በሚባል ሁኔታ እንቅስቃሴው ቀዘቀዘ።































በሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ጋብቻቸውን ከፈጸሙ በርካታ ምእመናን እና ምእመናት መካከል ጥቂቶቹ።




















































በሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ስመ ክርስትና ተቀበሉ ቁጥራቸው ከሦስት መቶ ከሚበልጡ ሕጻናት መካከል ጥቂቶቹ።

ክፍል ሁለት። የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን የገጠማት 
ከባድ ፈተና እና በፈጣሪ እርዳታ ፈተናውን ያለፈችበት ዘመን።

ይህ ወቅት ከላይ በክፍል አንድ የቤተክርስትያኗ ታሪክ በተተረከበት ታሪክ ማብቅያ ላይ እንደ ተገለጸው የቤተክርስትያናችን ሕልውና አደጋ የተጋረጠበት፣የበርካታ ምእመናን እና ምእመናንን ቅስም በሃዘን የሰበረ፣በአጠቃላይ በቤተክርስትያኑ አስተዳደር ላይ ተስፋው ተሟጦ ከቤተክርስትያን የሚመጣውን ማንኛውንም መልእክት ላለመስማት ጆሮውን የነፈገበት ግዜ ነው ማለት ይቻላል።ወደ ሃያ አመት ገደማ በተለያየ መንገድ ገቢ የነበራት ቤተ ክርስትያን በስጦታ ተገኘ የተባለውን ቤተ ክርስትያን የቤት ኪራይ ለመክፈል ከግለሰቦች ኪስ ተሰብስቦ እስከ መክፈል ደረሰች።

ምእመናን እና ምእመናት ባንክ ውስጥ ለቤተክርስትያን ማሰርያ  ከተቀመጠ መንካት ከማይቻለው አስራሰባት ሺሕ ዩሮ እና ወደ አስራ አንድ አመት ገደማ ሳይለወጥ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ምክትል ሊቀመንበር  ከሆነው ግለሰብ ጋር ቤተክርስትያናቸውን ተረከቡ።በዚህ አጋጣሚ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አባላት ከምክትል ሊቀመንበሩ እና ከገንዘብ ተቀባይዋ በስተቀር እነማን እንደ ሆኑ እና ኃላፊነታቸው ምን እንደ ሆነ በርካታ ምእመናን እና ምእመናት አያውቁም ነበር።ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ይልቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረው የቤተክርስትያን በአል አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት ይታወቁ ነበር።

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ምርጫም በአግባቡ ተከናውኖ ስለማያውቅ ነው አንድ  ግለሰብ ወደ አስራ አንድ አመት ገደማ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ምክትል ሊቀ መንበር ሆኖ ለመስራት የቻለው።ሁኔታዎች እንደ ተበላሹ ቢቀጥሉ ምርጫ ሳይከናወን አንድ ግለ ሰብ የእድሜ ልክ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ሊቀመንበር ሆኖ ሊሰራ እንደሚችል ምንም ጥርጥር አልነበረም።

በዚህ አጋጣሚ የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል አስተዳደሪ የሚደነቁት በሕግ መጠየቅ የሚገባውን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደርን ነጻ አድርገው የተፈጸመውን ስሕተት የእርሳቸው ብቻ አድርገው መቀበላቸው ነው።ከጥቂት የመቀዛቀዝ ሳምንታት በኋላ ምእመናን እና ምእመናት
" ቤተ ክርስትያናችንን እናድን!" በሚል ቁጭት መንፈስ በተደጋጋሚ በስብሰባ እየተገናኙ  ቤተክርስትያናቸው ከወደቀችብት የሚያነሱበትን መንገድ ለመቀየስ መወያየት ጀምሩ።በወቅቱ ቤተክርስትያኗን ያገለግሉ የነበሩት ቀሲስ መኮንን ከበደ እና ቀሲስ ዮሃንስ ከአሉት ዲያቆናት ጋር ተራ ገብተው በመቅደስ የእለተ ሰንበት ቅዳሴ ሳይታጎል መቀደስ ጀመረ።በምእመናን እና በምእመናትየቀድሞውን አስተዳዳሪ ኦዲት እንዲያደርግ  የተሰየመው የኦዲት ኮሚቴም ሪፖርቱን አቅርቦ ከጨረሰ በኋላ ሕጋዊ ጉዳዮችን እንዲከታተል የተሰየመው ኮሚቴ በሕግ በኩል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በነጻነት ለሕዝበ ክርስትያኑ መረጃ መስጠት ቀጠለ።በተለያየ ምክንያት ከቤተ ክርስትያን ርቀው የነበሩ ምእመናን እና ምእመናት ወደ ቤተክርስትያናቸው መመለስ ጀመሩ።ጥቂት መንፈሳዊ መነቃቃት እየታየ ቢመጣም በቀላሉ ከደረሰው ውድቀት  ማገገም ይቻላል ብሎ መገመት ዘበት ቢሆንም በተደጋጋሚ ስብሰባ ተገናኝቶ መወያየቱ ቀጥሎ ለመጀመርያ ግዜ በሦስት ቤተክርስትያናችንን ከውድቀት በሚያነሱ ወሳኝ ነገሮች ላይ 

፩ኛ/ ቤተክርስትያናችን በከተማው አስተዳደር ተመዝግባ ሕጋዊ ሆኖም ራሷ ችላ በምታወቅበት ሁኔታ ላይ

፪ኛ/የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቃል አዋዲን መሰረት ያደረገ እና ከምንኖርበት አገር ሕግ ጋር ተስማሚ የሆነ ሕግ በሚወጣበት ረገድ

፫ኛ/ ቤተክርስትያኗን በአስተዳዳሪነት የሚያገለግሉ የተሟላ የቤተክርስትያን እውቀት ያላችው አባት ለማምጣት ውሳኔ ተላለፈ።

ቤተ ክርስትያኗም በከተማው መስተዳደር ሕጋዊ ሆና ተመዘገበች።የቤተክርስትያኑም ሕገ ደንብ ረቂቅ ለመጀመርያ ተዘጋጅቶ ለሕዝበ ክርስትያኑ ለውይይት ቀርቦ ጸደቀ።

የቤተክርስትያን አስተዳዳሪ ለማምጣት የተደረገው ስብሰባ " ቄስ ይሻላል መነኩሴ?" በሚል ርእስ ላይ ከፍተኛ ክርክር ተደርጎ አብዛኞቹ ምእመናን እና ምእመናት የተለያዩ አሳማኝ ምክንያቶችን በማቅረብ በተለይ ወቅቱ ቀሳውስትን ከነቤተሰዎቻቸው ባለን የገንዘብ አቅም ማስተዳደር ስለማንችል መነኩሴ ቢሆን ይመረጣል የሚለው ሃሳብ አይሎ ስለ ወጣ በየአቅጣጫው ለቤተክርስትያናችን አስተዳዳሪ የሚሆኑ መነኩሴ የማፈላልግ ሥራ ተጀመረ።

ፈጣሪ ደግ ነው ለቤተክርስትያናችን እኛ ካዘጋጀነው መስፈርት የላቀ እውቀት ያላቸው የታወቁት አባት የወቅቱ ቆሞስ አባ ገብረ ሕይወት ፍሰሃ የዛሬው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ናትናኤል ከቅድስት አገር  ኢትዮጵያ  ወደ ሚዩኒክ መጥተው የሙኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ስራቸውን ጀመሩ።







ቆሞስ አባ ገብረ ህይወት ፍሰሃ የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዋና አስተዳዳሪ በነበሩበት ወቅት( አቡነ ናትናኤል)







ብፁእ ወቅዱስ  አቡነ ናትናኤል 

የአስተዳዳሪው በዚህ ወቅት መድረስ ለእርሳቸው ከበድ ያለ እና ውስብስብ የሆነ ስራ ቢጠብቃቸውም ለአብዛኛው የደብሩ  ምእመናን እና ምእመናት ከፍተኛ የእፎይታ ስሜት እንዲፈጠር አድርጎ ነበር።በመንፈሳዊ አገልግሎት ወቅት በምእመናን እና በምእመናት እጦት ተራቁቶ  የነበረው ቤተክርስትያን በሚገርም ፍጥነት ከአፍ እስከ ገደፉ መሙላት ጀመረ።የአስተዳዳሪው ሁለ ገብ ችሎታ ቤተክርስትያናችን መልሳ እንድታንሰራራ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ቢባል ምንም ማጋነን አይሆንም!አስተዳዳሪው በመጡ በአጭር ግዜ ውስጥ ወደ አስራ አንድ አመት ገደማ እንዲሁ በገደምዳሜ እየተደረገ አንድ ሰው የእድሜ ልክ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ምክትል ሊቀመንበር እስኪ መስል ድረስ ይደረግ የነበረውን ግልጽነት እና ተጠያቂነት የጎደለውን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አባላት ምርጫን አስወግደው ሁሉንም የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላትን ያሳተፈ ምርጫ እንዲከናወን አደረጉ።

ምርጫው በተከናወነ በአጭር ግዜ ውስጥ ከአዲሱ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ጋር እጅ እና ጓንት በመሆን የቅዱስ ገብርኤልን አመታዊ በአል ምክንያት በማድረግ ታላቅ የእርዳታ መርሃ ግብር በማዘጋጀት እና መርሃ ግብሩን እራሳቸው በመምራት ለሃያ አመታት ለቤተክርስትያን ማሰርያ የተሰበሰበው ገንዘብ ባክኖ እንጥፍጣፊ  እስራ ሰባት ሺሕ ዩሮ በቀረበት ወቅት በእለቱ ሁለት መቶ ሺሕ ዩሮ በመሰብሰብ የቤተክርስትያን ሕንጻ ማሰርያው ገንዘብ ወደ ሁለት መቶ አስራ ሰባት ሺሕ ዩሮ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
































ሪዝ ሽትራሴ በሚገኘው አዳራሽ የተዘጋጀው እና ሁለት መቶ ሺሕ ዩሮ ለቤተክርስትያን ሕንጻ ማሰርያ ገቢ የተገኘበት የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በአል ዋዜማ ከሞላ ጎደል ይህን ይመስል ነበር።

በዚህ ብቻ አላቆሙም!ቤተ ክርስትያናችን በተመሰረተችበት የመጀምርያዎቹ አመታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጎ በርካታ ገቢ ለቤተክርስትያን ሕንጻ ማሰርያ ገቢ ያስገባ የነበረው የቤተክርስትያን አሰሪ ኮሚቴ ከስሞ ስሙ በተረሳበት ወቅት በአዲስ መልክ የቤተክርስትያን ሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ ከአዲሱ ሰበካ መንፈሳዊ ጋር በመሆን እንዲመረጥ በማድረግ የቤተ ክርስትያን አሰሪ ኮሚቴው  ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር የሁለተኛ ዙር እርዳታ አሁንም የቅዱስ ገብርኤልን አመታዊ በአል ምክንያት በማድረግ እንዲዘጋጅ አድርገው መቶ ስልሳ ሺሕ ዩሮ ለቤተ ክርስትያን ሕንጻ ማሰርያ ገቢ በማስገባት በጀርመን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስትያናት ታሪክ ታይቶ እና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሁለት ቀን ባእላት ሦስት መቶ ስድሣ ሺሕ ዩሮ ለቤተክርስትያን ማሰርያ እርዳታ በመሰብሰብ የማይረሳ የታሪክ አሻራ ለማስቀመጥ ችለዋል።ይህ ወቅት ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ተወያይቶ መስራት ፣ምእመናን እና ምእመናት ሳይፈሩ ሃሳባቸውን መግለጽ እና የቤተ ክርስትያናችን ጉዳይ እኛንም ያገባናል ብለው ቤተ ክርስትያናቸውን ለመደገፍ እና ለመጠበቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደረጉቡት ወቅት ነው ቢባል በፍጹም አልተጋነነም።የደብር አስተዳዳሪ እና የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ተባብረው መስራት ከቻሉ ቤተክርስትያናችን ማደግ እንደምትችል ትምህርት ያገኘንበትን ወቅት መቼም የሚዘነጋ አይደለም።የሚዩኒክ ሕዝብም መልካም እረኛ ካገኘ እንዴት ቤተክትስትያኑን መጠበቅ እና ማሳደግ እንደሚችል የተገነዘበበትን ወቅት በአጭር ግዜ ውስጥ እንደማይረሳው የታመነ ነው።ይህ ግዜ መንፈሳዊ አገልግሎቱ ጠንክሮ ቅዳሴው፣ ማሕሌቱ፣ስአታቱ፣ የሰርክ ጸሎቱ፣ስብከተ ወንጌሉ፣የሕጻናቱ ዝማሬ እና ትምሕርቱ ምኑ ቅጡ ቤተክርስትያናችን እንደ ገና የለመለመችበት ግዜ ነበር።በተለይ የወቅቱ የቤተ ክርስትያናችን አስተዳዳሪ በመጡበት ዘመን አይተን የማናውቀውን ዛሬ ድረስ በሰሞነ ሕማማት በደብራችን ውስጥ በአመት በአመት በዜማ የሚደረገውን ምስጋና ለፈጣሪ በማቅርብ በችሎታቸው ያስደመሙን ሲሆን በወቅቱ ምእመናን እና ምእመናት ከደስታቸው ብዛት ማንም ሳይጠይቃቸው ለአስተዳዳርያችን እክፋይ በማዘጋጀት በመሸለም ደስታቸውን ሊገልፁ ችለዋል።















የሆሳእና ክብረ በአል ከአባ ገብረሕይወት( ብጹእ አቡነ ናትናኤል) ጋር።



















ሰሞነ ሕማማት ከአባ ገብረ ሕይወት( ብጹእ አቡነ ናትናኤል) ጋር።












ጸሎተ ሐሙሥ 










የጌታችን እና የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት



























በአል በድምቀት ሲከበር።







የትንሳኤ በአል አከባበር።

ከዚህ በፊት ያለ ሥራ የባከኑትን ግዚያት የቤተ ክርስትያን ሕንጻ አሰሪ ኮሚቴው ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ተጨማሪ የቤተክርስትያን ሕንጻ ማሰርያ ገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን በመቀየስ ገቢ ከማስገኘቱ ጎን ለጎን  በሦስት አቅጣጫ የደብሩ ንብረት የሆነ የሕንጻ ባለቤት ለመሆን ጥረቱን ጀመረ።

፩ኛ/ ከካቶሊክ ቤተክርስትያን ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነት በማጠናከር የማይገለገሉበትን ሕንጻ ቤተ ክርስትያን ካለ ገዝቶ የእራስ ንብረት ለማድረግ።

፪ኛ/ከኢቫንጀሊካል ቤተክርስትያን ጋር ያለንን የጠበቀ ወዳጅነት መሰረት በማድረግ በአሁን ሰአት በኪራይ ከእነርሱ አግኝተን የምንገለገልበትን ሕንጻም ይሁን ሌላም ሕንጻ በመግዛት የግላችን ሕንጻ ቤተክርስትያን እንዲኖረን 

፫ኛ/ በነጻው ገበያ ውስጥ ፍለጋ በማድረግ ሕንጻ ለመግዛት አለያም ባዶ የከተማ ቦታ ገዝቶ ቤተክርስትያን ለመስራት ስራውን በፍጥነት ጀመረ።

ይሁን እና የቤተ ክርስትያን አሰሪ ኮሚቴው ሕንጻ ለማግኘት የሚያደርገውን ያላሰለሰ ጥረት የሚያደናቅፉ ነገሮች።መከሰታቸው አልቀረም።

፩ኛ/ሕንጻ ተገኝቶ ለጠቅላላ ጉባኤ ለስምምነት እስኪቀርብ ድረስ የተገኘው ሕንጻ በሌሎች ገዢዎች መወሰዱ።

፪ኛ/ በአብዛኛው ቤተክርስትያን ሊሆኑ የሚችሉ  ሕንጻዎች የሚገኙት ከሚዩኒክ ከተማ ወጣ ብለው ሲሆን ርቀታቸው ለሕዝበ ክርስትያኑ ተስማሚ ባለመሆኑ።

፫ኛ/ሕንጻው ተገኝቶ ለመግዛት ፍላጎት ቢኖርም ሕንጻው የተገኘበት ቦታ የከተማ ፕላን ክፍል ፈቃድ በመከልከሉ።በተለይ በሦስተኛው ምክንያት የተነሳ ለቤተክርስትያን የሚሆን ሕንጻ ከሚዩኒክ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ ዳሃው በምትባል ከተማ ልዩ ስሟ ፊርኪርሸን በምትባል መንደር በአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዩሮ አግኝቶ የከተማው አስተዳደር ሳይስማማ ቀርቶ ከእጅ ያመለጠው ሕንጻ ዛሬም ድረስ በቁጭት ሲታሰብ ይኖራል።

ከዋጋው ማነስ እና ከሕንጻው ትልቅነት አኳያ ስጦታ ተገኝቶ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።

፬ኛ/ በሚዩኒክ ከተማ ከሌሎች የጀርመን ግዛቶች ጋር ሲነፃጸር ሕንጻ እና ባዶ ቦታ መግዛት ከዋጋው ውድነት አኳያ በጣም ከባድ በመሆኑ ወዘተ ናቸው።

ይሁን እና የቤተ ክርስትያን አሰሪ ኮሚቴው ሕንጻ ወይም ባዶ ቦታ ማግኘቱ ቢከብድበትም ወደ ፊት ሕንጻ ተገኝቶ ቢገዛ ሊመጣ የሚችለውን እዳ ለመቀነስ የተለያየ የገቢ ዘዴዎችን በመቀየስ እንቅስቃሴ ከማድረግ ተገትቶ አያውቅም።















































እንደ ኤ:አ በየካቲት ፬ ሁለት ሺሕ አስራ ሰባት የተደረገው ቤተክርስትያናችንን የማስተዋወቅ እና የገቢ ማስገኛ ዝግጅት ከሞላ ጎደል ይህን ይመስል ነበር።

በተለይ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት

፬ ሁለት ሺሕ አስራሰባት የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴው እና የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ በመተባበር ቤተክርስትያናችንን ለማስተዋወቅ እና ገቢ ለማስገኘት ያዘጋጁት ዝግጅት የላቀ ስፍራ የሚሰጠው ሲሆን በእለቱ ዝግጅቱን የመካፈል እድል የገጠማቸው አውሮፓውያን እንግዶች በዝግጅቱ ከመደሰታቸው የተነሳ ይህን መሰል ዝግጅቶችን ደጋግመን አዘጋጅተን እንድንጋብዛቸው በመጠየቅ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ባሳለፍናቸው የቤተ ክርስትያናችን ገጠመኞች በርካታ አስደናቂ ተግባራት የተፈጸሙ ሲሆን በተለይ ወንድማችን ቀሲስ ዮሃንስ ወደ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ በተጓዘበት ወቅት ድንገተኛ የጤንነት እክል ገጥሞት እርሱን ወደ እሚኖርበት ወደ ጀርመን አገር ለማምጣት የደብራችን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር የደብሩን ምእመናን እና ምእመናት፣ በሌላ የጀርመን ግዛቶች የሚገኙ ሕዝበ ክርስትያንን ጭምር በማስተባበር፣በሙንሽን የሚገኙ የመረዳጃ እድሮችንም በማሳተፍ ያደረገው ርብርብ ሁል ግዜም በቀሲስ ዮሃንስ ቤተሰቦች እና በሕዝበ ክርስትያኑ ሲታወስ ይኖራል። ቀሲስ ዮሃንስን ከአዲስ አበባ ወደ ሚዩኒክ ከተማ  ለማምጣት ለመጓጓዢያ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በሁለት ቀን ውስጥ ከስልሳ ሺሕ ዩሮ በላይ በመሰብሰብ ቀሲስ ዮሃንስን ከአዲስ አበባ ወደ ሚዩኒክ በተለየ የሕክምና አውሮፕላን እንዲመጣ በማድረግ ሕዝበ ክርስትያኑ ለቤተክርስትያን አገልጋዮች ያለውን ክብር እና ፍቅር የሚያስመሰክርበትን ታላቅ ተግባር ፈጽሟል።

ሌላው በቤተክርስትያናችን የረጅም ዘመን ታሪክ ከበርካት ገጠመኞች መካከል በዘግናኝነቱ የማይዘነጋው  በ     በሐምሌ  ወር የቅዱስ ገብርኤልን ዓመታዊ በአል ለማክበር በዝግጅት ላይ እንዳለን ከደብራችን በግምት ወደ ሦስት መቶ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ማክ ዶናልስ ፈጣን ምግብ መሸጫ ውስጥ የተደረገው የግድያ ወንጀል ነው።በእለቱ በተከሰተው ማሳካር ተደናግጠው በመሸሽ ላይ የነበሩ የከተማው ነዋሪዎችን ተጨማሪ የሰው ደም እንዳይፈስ እና ሕይወት እንዳይቀጠፍ ቤተክርስትያናችን መከታ በመሆን የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ታድጋለች።በዚህ ነብስ አድን ተግባር ከተለያዩ ተቋማት እና በቤተክርስትያን ተጠልለው ሕይወታቸውን ማትረፍ ከቻሉ ሰዎች ቤተሰቦች የላቀ ምስጋና ቤተክርስትያናችን ማግኘት ችላለች።



































ግድያው በተፈጸመበት እለት በቤተክርስትያን ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ሰዎች ይህን ይመስሉ ነበር።













ግድያው በተፈጸመበት ስፍራ የደብራችን አስተዳዳሪ  ቆሞስ እባ ገብረ ሕይወት ፍስሃ ( ሊቀ ጳጳስ አቡነ  ናትናኤል)  ተገኝተው የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ ሃዘናቸውን ሲገልጹ።







ግድያው ከተፈጸመ ከጥቂት ቀናት በኋላ የቅዱስ ገብርኤልን አመታዊ በአል በተከረበት እለት ቤተክርስትያናችን ግድያው በተፈጸመበት ወቅት በአካባቢው የነበሩ የከተማ ነዋሪዎችን ነፍስ
ለማዳን ያደረገችውን ጥረት በማድነቅ የኢቫንጀሊካል ቤተክርስትያን ተወካይ ዲያኮን ፍሬይ ምስጋና ሲያቀርቡ።

ቤተ ክርስትያናችን ከሌሎች አገራት አብያተ ክርስትያናት ጋር ያላት ግንኙነት የበለጠ እንዲዳብር እና እንድትታወቅ የረዳት ሲሆን በመስኩ የሚደረገውን ማንኛውንም ክርስትያናዊ ወንድማማችነት የሚጠይቀውን ተግባር በመፈጸም ከበሬታ ልታገኝ ችላለች።

በተለይ በጀርመን አገር የተወለዱ ሕጻናት በሌላ እምነት እንዳይጠመዱ፣ ሃይማኖታቸውን፣ትውፊታቸውን እየተረዱ እንዲያድጉ የተደረገው ጥረት በጣም አመርቂ ሲሆን ሕጻናትን በእድሜ በመከፋፈል የሃይማኖት፣ የንባብ፣የጽሁፍ እና የመዝሙር ትምህርት በመስጠት የተለያዩ መርሃ ግብራትን መንፈሳዊ ጉዞዎችን የመሳሰሉትን  በማዘጋጀት፣የሚሰጠውን ትምህርት ያጠናቀቁትን የምስክር ወረቀት በመስጠት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ኖረዋል።በተለይ በደብራችን ካሕን በቀሲስ ዶክተር አምሳሉ እና በዲያቆን አዳም ሊበን ተጀምሮ የነበረው ከአስራ አራት አመት በላይ ለሆኑ ወጣቶች በጀርመንኛ ቋንቋ ይሰጥ የነበረው የሃይማኖት ትምህርት በወጣቶቹ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር።







የአንደኛ ድረጃ ትምህርት ለሚጀምሩ ሕጻናት እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት የደብሩ አስተዳዳሪ ለሕጻናቱ ሽልማት በማበርከት ላይ ሳሉ።












የሃይማኖት፣ የጽሁፍ እና የንባብ ትምህርት ያጠናቀቁ ሕጻናት የምረቃ ሥነ ስርአት።






ሕጻናትን የማገናኛ መርሃ ግብር።







ሕጻናት እንዲገናኙ በሚዘጋጅላቸው መርሃ ግብር ላይ በዝማሬ ላይ ሳሉ።







መንፈሳዊ ጉዞ።

የአገልጋይ ካህናት እና ዲያቆናት መበርከት በደብራችን ውስጥ ያለውን የአገልጋይ ካሕናት እና ዲያቆናትን እጥረት በማስወገድ ረገድ ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመገንዘብ የደብሩ አስተዳዳሪ ሁለት ታዳጊዎችን የአብነት ትምህርት በመስጠት በዲያቆንነት እንዲያገለግሉ ያደረጉ ሲሆን ለረዥም ግዜ በዲቁና ያገለገሉትን ዲያቆን ዶክተር አምሳሉን ወደ ቅስና ማእረግ ከፍ በማድረግ ቤተክርስትያናችን የምትሰጠው አገልግሎት እንዲሰፋ ተደርጓል።በተለይ ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ለትምህርት እና ለምርምር ስራ ጀርመን አገር  መጥተው በዚህ በታሪካዊ ደብር ክህነት መቀበላቸው አስደሳች አጋጣሚ ሲሆን ቤተክርስትያንን በማገልገል ያሳዩት ትጋት በሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ምእመናን እና ምእመናት፣ በደብሩ አገልጋይ ካህናት እና ዲያቆናት ዘንድ ሲታወስ ይኖራል።











ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ በብፁእ አቡነ ሙሴ ክህነት ሲቀበል።











ወጣት አላዛር የዲቁና ማእረግ ከብፁእ አቡነ ሙሴ ሲቀበል።











ታዳጊ ወጣት አዳም ሊበን ከብፁእ አቡነ ሙሴ የዲቁና ማእረግ ሲቀበል።















የሚዩኒክ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል አገልጋይ ካሕናት እና ዲያቆናት።











የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በአል።

















የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር እባላት ከ2012 እስከ 2014 ዓ: ም።










የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አባላት ከ2015 እስከ 2018 ዓ፡ም











ዶክተር ዘውዱ ውብእንግዳ በሞት ከመኃከላችን ብትለየንም ለሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ  ገብርኤል ቤተክርስትያን ያደረግኻቸውን መልካም ተግባራት በእኛ ዘንድ ሲታወሱ ይኖራሉ።

 
ክፍል ሦስት።አባ ገብረ ሕይወት (አቡነ ናትናኤል) ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ ከሄዱ በኋላ
እና የወቅቱ የደብራችን አስተዳዳሪ ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናው ከመጡ በኋላ ያለውን እንቅስቃሴ ያጠቃለለ።

ይህ ወቅት ብፁእ አቡነ ናትናኤል( አባ ገብረ ሕይወት) ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ በድንገት ከእኛ የተለዩበት ግዜ በመሆኑ የጉዟቸው ጉዳይ ቤተክርስትያናችንን ይጎዳዋል የሚል ትልቅ ጥርጣሬ ተፈጥሮ ውስጥ ለውስጥ የተብላላበት ግዜ ቢሆንም በተለይ እንደ እርሳቸው ያለ አስተዳዳሪ አናገኝም የሚለው ፍራቻ በጣም የነገሰበት ግዜ ነበር።በወቅቱ የነበረው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አስቸኳይ ለደብራችን ተስማሚ የሆኑ መነኮሳትን የመምረጥ እና የማወዳደር ስራ ሊሰሩ የሚችሉ ሰዎችን በማዘጋጀት ስራው በተቀላጠፈ ሁኔታ ወደ ፊት መራመድ ችሎ ለአስተዳዳሪነት ከቀረቡት መነኮሳት መካከል በማንኛውም መስፈርት ለደብራችን ይመጥናሉ ያላቸውን ሦስት መነኮሳት በመለየት ለጠቅላላ ጉባኤው ለውሳኔ አቀረበ።ጠቅላላ ጉባኤውም በእጩነት ከቀረቡት ሦስቱ መነኮሳት መካከል የአሁኑን የደብራችን አስተዳዳሪ ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ያሬድን ምስጋናውን በቀረበው መስፈርት መሰረት በከፍተኛ ድምጽ መርጦ የደብራችን አስተዳዳሪ እንዲሆኑ ወሰነ።በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ መሰረት አስተዳዳሪው ከቅድስት አገር ኢትዮጵያ ወደ ጀርመን አገር ሚዩኒክ ከተማ የሚመጡበት ስራ ሀተብሎ ተጀመረ።ይሁን እና አገር ቤት በነበረው ቢሮክራሲ መክፋት አስተዳዳሪውን ለማምጣት የተደረገው ጥረት አንድ አመት ሊፈጅ ችሏል።

በዚህ ግዜ ነው እንግዲህ ያለ አስተዳዳሪ ያለችውን ቤተ ክርስትያን በማስተዳደር ረገድ በወቅቱ እነበረው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት የወደቀው።

አስተዳዳሪው ከኢትዮጵያ የሚመጡበትን መንገድ ጎን ለጎን እያከናወነ ምንም ነገር ሳይጓደል የሚያስደንቅ የአስተዳደር ብቃት በማሳየት ቤተክርስትያኑን ለዛሬው የደብራችን አስተዳደሪ ሊያስረክብ ችሏል።ይህ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር በዚህ በአንድ አመት ውስጥ ከሰራቸው ታላላቅ ስራዎች መካከል 

፩ኛ/ ብዙ ነገር ይጎለው የነበረውን የደብራችንን የመተዳደርያ ሕገ ደንብ አንድ የባለሙያዎች ኮሚቴ በማቋቋም ሕገ ደንቡን እንዲያሻሽሉ በማድረግ የተሻሻለውን ሕገ ደንብ ለውይይት እና ለውሳኔ ለጠቅላላ ጉባኤው አቅርቦ ያጸደቀ ሲሆን።

፪ኛ/ ከቤተክርስትያን አሰሪ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ዳሃው አካባቢ ልዩ ስሙ ፊርኪርሸን በሚባል ስፍራ ሕንጻ ቤተክርስትያን ለመግዛት ያደረገው ከፍተኛ ጥረት በወቅቱ ቤተክርስትያኑን ለመግዛት የሚወሰደውን ክሬዲት ለመክፈል በአጭር ግዜ ውስጥ ቁጥራቸው መቶ ሃምሳ የሚሞሉ የደብራችን ሰበካ ጉባኤ  አባላትን ለማሳተፍ ተችሎ ነበር።

፫ኛ/የደብራችን ተማሪ ሕጻናት እየበዙ ስለመጡ በአንደኛ ፎቅ ላይ የሚገኘውን የመዋለ ሕጻናት እሁድ እሁድ እንድንገለገልበት በመከራየት የነበረውን የመማርያ ስፍራ እጥረት ማስወገድ ችሏል።

፬ኛ/ለሦስተኛ ግዜ የተደረገውን የቤተክርስትያን ማሰርያ አስተዋጽኦ ለማሰባሰብ የአመቱ የቅዱስ ገብርኤልን ዋዜማ በአል ዝግጅትን  እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የተደረገውን ተግባር እንዲሳካ ከቤተክርስትያን አሰሪ ኮሚቴው ጋር በመተባበር ያደረገው ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር።

በዚህ የገቢ ማሰባሰብያ ዝግጅት ላይ ለመጀመርያ ግዜ በመገኘት ምእመናን እና ምእመናት የአስተዋጽኦ እጃቸውን እንዲዘረጉ አጠር ያለ የማነቃቅያ ትምህርት የደብራችን አስተዳዳሪ ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ያሬድ የሰጡ ሲሆን በአውሮፓ የመጀመርያ የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በአልን ዋዜማ በማክበር የተሳተፉበት ለእርሳቸውም ለሚዩኒክ ምእመናንም የማይረሳ ቀን ነው።በእለቱም ወደ ሰማንያ አምስት ሺሕ ዩሮ ለመሰብሰብ ተችሏል።

፭ኛ/በአገር ቤት ያለውን ቢሮክራሲ በጣጥሶ ጠቅላላ ጉባኤው የመረጣቸውን አስተዳዳሪ ለማምጣት በሦስት አባላት የተዋቀረ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ አስተዳዳሪያችን እንዲመጡ ያደረገው ጥረት ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።

ከላይ እንደተገለጸው በሁለት ካህናት እና በአንድ ምእመን  ምለትም  በቀሲስ ያሬድ፣ በቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ እና በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ምክትል ሊቀመንበር በአቶ እስጢፋኖስ ብሥራት የተዋቀረው ቡድን የተላከበትን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት የአስተዳዳሪው ወደ ሚዩኒክ የማምጣቱን ተግባር ሊያፋጥነው በመቻሉ ሦስተኛው የሚዩኒክ ቅዱስ ገብርኤል ደብር አስተዳዳሪ እንደ ፍላጎታችን ሊመጡ ችለዋል።ቤተ ክርስትያናችን ያለ አስተዳዳሪ ለመቆየት በተገደደችበት ወቅት ቀሲስ ያሬድ እና ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ቤተክርስትያናቸውን ከሚወዱት ዲያቆናት ጋር በፈረቃ በመቀደስ እና የሚጠበቅባቸውን መንፈሳዊ ትጋት  በማሳየት ሕዝበ ክርስትያኑን  ለማገልገል ያደረጉት ትጋት የሚያስመሰግናቸው ነው።በተለይ ዶክተር ቀሲስ አምሳሉ እንደተገለጸው ለምርምር ስራ ወደ ሚዩኒክ የመጡ ሲሆን ጎን ለጎን በተለያዩ ቤተክርስትያኗን ይጠቅማታል ብለው በሚያምኑበት አገልግሎት በሙሉ በንቃት እና  በፍላጎት ያሳዩት የነበረው ተሳትፎ ሁሌም እንድናስታውሳቸው ያስገድደናል።በተለይ ጠዋት ከቅዳሴ በኋላ አውደ ምህረት ላይ ከሚያስተምሩት ትምህርት በተጨማሪ ለምእመናን ተጨማሪ የትምህርት ክፍለ ግዜ በማዘጋጀት ሰንበት ክርስትያንን ቤተሰቤ ሳይሉ ለምእመናን ቃለ እግዚአብሔር በማስተማር ጊዝያቸውን በቤተክርስትያን ያሳልፉ እንደ ነበር የሚዩኒክ ምእመናን ምስክሮች ናቸው።በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ከዲያቆን አዳም ጋር በመሆን ከአስራ አራት አመት በላይ የሆኑ ወጣቶችን በቤተ ክርስትያን በማሰባሰብ ወጣቶቹ ስለ ቤተክርስትያናቸው እና ስለ ሃይማኖታቸው እውቀት እንዲኖራቸው ያደረጉት ጥረት ሌላው ቀሲስ ዶክተር አምሳሉን እንዳንረሳቸው የሚያደርገን ምክንያት ነው።



























የደብራችን ወጣት ምእመናን እና ምእመናት የሃይማኖት ትምህርት ሲከታተሉ።

ሌላው ለሶስተኛ ግዜ የደብራችን ሕገ ደንብ ሲሻሻል የአሻሻዩ ኮሚቴ አባል በመሆን ሕጉን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ዶክተር አምሳሉ የምርምር ስራቸውን ፈጽመው ወደ አገር ቤት በተመለሱ ወቅት የደብራችን ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናው፣በርካታ ምእመናን እና ምእመናት፣ሕጻናት በተገኙበት በድምቀት በተከናወን ከፍተኛ የሽኝት ዝግጅት ልንሰናበታቸውም ችለናል።
















የቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ እና የቤተሰቦቻቸው የሽኝት ዝግጅት ከሞላ ጎደል ይህን ይመስል ነበር።

በእለቱ የቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ሁለት ሕጻናት ልጆቻቸው ጓደኞች ከቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ልጆች በመለየታቸው ክፉኛ አልቅሰው ሕዝበ ክርስትያኑንም ጭምር አስለቅሰውታል።

ይህቺ ታሪካዊ ደብራችን እንደ አጋጣሚ ሆኖ እግዚአብሔር የሊቃውንት መፈራረቅያ አድርጓት ብፁእ አቡነ ናትናኤል ( አባ ገብረ ሕይወት ፍሰሃ) ደብራችንን ትተዋት ቢሄዱም በሁሉም የቤተክርስትያን እውቀት  ምሉእ የሆነ ብቃት ያላቸው እና ታላቁን የቅዱስ  ላልይበላ ገዳምን ያስተዳደሩትን  ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ያሬድን ምትክ አግኝታ  ቤተክርስትያናችን በሁሉም አቅጣጫ አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት ቀጠለች።


 





የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዋና አስተዳዳሪ የቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናው አቀባበል በሚዩኒክ አውሮፕላን ማማረፍያ።














የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዋና አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናው።









ለሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዋና አስተዳዳሪ ለቆሞስ አባ ያሬድ ምሥጋናው የጀርመን እና የአካባቢው አገራት አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁእ አቡነ ዲዮናሲዮስ በተገኙበት አቀባበል ሲደረግ።






የቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናው አቀባበል በከፊል።










ቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናው በሮም ቅድስት ማርያም እና በቅዱስ ኡራኤል ዋና አስተዳዳሪ ግብዣ ወደ ሮም በሄዱበት ወቅት በቫቲካን ጉብኝት ላይ።

ጉባኤው ሰፋ!ትምህርቱም ተስፋፋ!

በዚህ አጋጥሚ መዘንጋት የሌለበት ሌላው ነገር ለረዥም ግዜ አስፈላጊነቱ ተዘንግቶ የቆየው የቤተ ክርስትያን አሰሪ ኮሚቴ ተመርጦ ያከናወናቸው ተግባራት ናቸው።

ሕንጻ ቤተክርስትያን በመፈለግ ረገድ ስትራተጂ በመቀየስ በተለያዩ አቅጣጫዎች ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ጋር የፈጸማቸው ተግባራት ኮሚቴውን የሚያስመሰግኑ ሲሆኑ ለቤተክርስትያን የሚሆን ሕንጻ ለመግዛት ጫፍ ላይ ደርሶ ከከተማ አስተዳደሩ ይሁንታ በማጣት የሕዝበ ክርስትያኑን ሕንጻ ቤተክትስትያን የማግኘት ፍላጎት ላያሳካ ጥረት አድርጎ ሳይሳካለት ቀርቷል።ይሁን እና በርካታ የገቢ ማሰባሰብያ ዝግጅቶችን ከሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር አዘጋጅቶ የደብራችን ሕንጻ ማሰርያ ካፒታል እንዲዳብር በማድረግ፣ከካቶሊክ እና ከኢቫንጀሊካል አብያተ ክርስትያን ጋር ዲፕሎማስያዊና የክርስትና ወንድማማች ግንኙነት በመፍጠር ሕንጻ ቤተክርስትያን ለማግኘት ያደርግ የነበረው ጥረት እርሱን ለተካው የቤተክርስትያን ሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ ፈር ቀዳጅ ለመሆን በቅቷል።ይሕ ሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ ደብራችን አስተዳዳሪ ባልነበራት ወቅት የሥራ ዲሲፕሊንን በማክበር እንደ ሰበካ ጉባኤ መንፈሳዊ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ ችሏል።

የደብራችን አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናው አጋጣሚ ሆኖ የመጡበት ግዜ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ እና የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴው የስራ ዘመን መገባደጃ በመሆኑ ብዙም ግዜ ሳይወስዱ አካባቢውን በመለማመድ ሁለቱንም ኮሚቴዎች እና ለመጀመርያ ግዜ በደብራችን ታሪክ የተቋቋመውን የሕግ ክፍል አባላትን በማስመረጥ እርሳቸውን ጨምሮ በአስራ አንድ ሰዎች ከተጠናከረው አዲሱ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ጋር ስራቸውን ጀመሩ።የተለያዩ ንኡሳን ኮሚቴዎችን የነበሩትን በማጠናከር ያልነበሩትን በመመስረት  ደብራችን የጎደለውን ነገር ለማሟላት ጥረታቸውን ቀጠሉ።በተለይ የራሳችን ሕንጻ ቤተክርስትያን ለማግኘት በሚደረገው በእያንዳንዱ ጥረት ውስጥ እንደ አንድ ኮሚቴ አባል በመሳተፍ የሚያሳዩት ትጋት ብንጠቅስ ውዳሴ ከንቱ እንደማይሆን እርግጠኛ መሆን ይቻላል።በማንኛውም የአየር ጸባይ ሕንጻ ቤተክርስትያን ተገኘ ሲባል ለማየት በረደኝ ሞቀኝ ሳይሉ እስፍራው በመድረስ የሚያሳዩት ቤተክርስትያን የማግኘት ፍላጎት በእውነት የሚደነቅ ነው።ቤተክርስትያን ሊያስገኝ የሚችል መረጃ እና መንገድ ሲገኝ ከኮሚቴው ጋር ቀጠሮ ይዘው ውይይት እንዲደረግ የሚያመቻቹት ነገርም ሌላው ተጠቃሽ ነገር ነው።ሕንጻ ቤተ ክርስትያን ለማግኘት ከሌሎች አብያተ ክርስትያናት ጋር በተደረጉ በሁሉም  ንግግሮች ላይ በመሳተፍ ሕንጻ ቤተክርስትያን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በማበርከትም ላይ ይገኛሉ።

በተለይ የመጀመርያው የደብራችን የሚዲያ ኮሚቴ ቀደም ብሎ ያሳይ የነበረው የነቃ ተሳትፎ ተዳክሞ ወደ መዘንጋት በደረሰበት ወቅት ከሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ሚዲያ ኮሚቴውን በአዲስ መልክ በአስራ ሰምንት አባላት በመመስረት እና በሚያስፈልገው የአገልግሎት መሳርያ በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

በደብራችን ታሪክ ለመጀምርያ ግዜ በሦስት አባላት የተቋቋመውም የሕግ ክፍልም በደብራችን ሕገ ደንብ ውስጥ ይጎድላሉ ያላቸውን የሚጠቅሙ ሕግጋቶችን በማዘጋጀት ስራውን የጀመረ ሲሆን ወደ ፊት ሕገ ደንቡ ውስጥ እንዲካተቱ ጥናቱን ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላው የንብረት ክፍልን የአሰራር አደረጃጀት በከፊል ይታዩ የነበሩትን የተዝረከረኩ እና በተለይ ጥገናዎችን በተመለከተ ይስተዋል የነበረውን ባለቤት ያልነበረውን አሰራር በማስወገድ ሥርአት እንዲይዝ ለማድረግ የተደረገው ጥረት  እና ግልጽነት መሰረት ያደረገ አሰራር የቤተክርስትያንን ወጪ በመቀነስ ረገድ ጥሩ ሚና እንዲጫወት ረድቷል።

የሕጻናት ትምህርት የሚስፋፋበትን መንገድ በመቀየስ ረገድ ከፍተኛም ስራ ተሰርቷል።






ታዳጊ ሕፃናት የጌታን ልደት ዋዜማ በመዝሙር ሲያከብሩ።

ሕጻናት ሃይማኖታቸውን፣ የቤተ ክርስትያናቸውን ትውፊት እያወቁ እንዲያድጉ፣ በደብሩ ካሕናት በተለይ በአስተዳዳሪው በኩል የአብነት ትምህርት ለተወሰኑ ሕጻናትም የሚሰጥ ሲሆን የአብነት ትምህርቱን ውጤት የደብራችን ምእመናን ለማጣጣም ችለዋል።

ዛሬ አለማችንን ያናወጠው የኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሺኝ ከመከሰቱ በፊት የደብራችን አስተዳዳሪ በመጡበት የመጀምርያ አመት በሁሉም መስክ የተደረጉት እንቅስቃሴዎች እያደጉ መጥተው በተለይ የቀደመውን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር ፈለግ በመከተል በአንድ አመት ውስጥ ከአስተዳደራዊ ስራ የተረፈ መቶ ሺሕ ዩሮ ወደ ቤተ ክርስትያን ማሰርያ የባንክ አካውንት በማስገባት አስደናቂ ተግባር የተፈጸመ ሲሆን በቅርቡ የቤተክርስትያናችን ገቢ በኮቪድ አስራ ዘጠኝ በቀነሰበት ወቅት ከአስተዳደራዊ ስራ የተረፈውን ሃምሳ ሺሕ ዩሮ ወደ ቤተክርስትያን ማሰርያ የባንክ አካውንት ውስጥ ለማስገባትም ተችሏል።ይህ መረጃ የደብራችን እድገት ምን አይነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ የሚመሰክር ሲሆን የደብራችን ምእመናን እና ምእመናት በደብራቸው ላይ ያላቸውን እምነት እና መተማመን ሊገልጽ የሚችል ማስረጃ ነው።የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በአል ከተለያዩ የጀርመን ግዛቶች እና ጎረቤት አገሮች በአሉን ለመካፈል ከሚመጡ ምእመናን እና ምእመናት ጋር በድምቀት ተከብሯል።ልዩ መንፈሳዊ እርካታ በሚሰጥ እና በረከት በሚያስገኝ ሁኔታ የትንሳኤ በአል እና የጌታ ልደት በአል ተከብረዋል።

በሌሎች ብዙ አድባራት ባልተለመደ ሁኔታ እነደ አንድ ታላቅ ገዳም ሰሞነ ሕማማትን በዜማ እና በደብራችን አስተዳዳሪ ቅዱሳት መጽሃፍት እየተተረጎሙ በጥሞና ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ምእመናን እና ምእመናት የበረከቱ ተሳታፊ ለመሆን በቅተዋል።







21 April 2019 የሆሳእና ክብረ በአል።








27 April 2019 የትንሣኤ ዋዜማ ማሕሌት።

ዘመነ ጽጌ ተጀምሮ እስኪፈጸም እንደ አንድ ታላቅ ገዳም ዘወትር ቅዳሜ ሌሊት ማሕሌት በመቆም ምእመናን እና ምእመናት የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በድምቀት መከበሩ የደብራችንን አስተዳዳሪ፣የደብራችን አገልጋይ ካሕናት፣ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅዱስ ኡራኤል የመጡ ካህናት እና ዲያቆናትን ትጋት ያስመሰከረ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።





























































ዘመነ ጽጌ ዘወትር ቅዳሜ ሌሊት ይህን በመሰለ ሁኔታ በማሕሌት በድምቀት ይከበር ነበር።

 ጾመ ፍልሰታን መምሕራን ከአገር ቤት በማስመጣት፣ አስራ ስድስቱን ቀናት በደብራችን አስተዳዳሪ የውዳሴ ማርያም ትርጉም እየተሰጠ፣ ከንጋቱ እስራ አንድ ሰአት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰአት የጸሎት መርሃ ግብሮቹን እና ቅዳሴውን በመፈጸም ምእመናን ከዚህ ቀደሙ ለየት ባለ ሁኔታ መንፈሳዊ  አገልግሎት መስጠት ተችሏል።ዘመነ ጽጌ ተጀምሮ እስኪፈጸም እንደ አንድ ታላቅ ገዳም ዘወትር ቅዳሜ ሌሊት ማሕሌት በመቆም ምእመናን እና ምእመናት የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተደረገው ጥረት የደብራችንን አስተዳዳሪ፣አገልጋይ ካሕናትን እና ዲያቆናትን የሚያስመሰግን ነው።









የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል አስተዳዳሪ በጾመ ፍልሰታ ውዳሴ ማርያምን ለምእመናን እና ለምእመናት ሲተረጉሙ። 

ርእሰ አውድ አመትን (ዘመን መለወጫን) በአስደሳች ሁኔታ በርካታ ምእመናን እና ምእመናት በተገኙበት እንደተለመደው አገር ቤትን በሚያስታውስ ሁኔታ መከበሩ የቀጠለ ሲሆን










ደብረ ታቦር ከኮቪድ አስራ ዘጠኝ በፊት በድምቀት ሲከበር።










የቅዱስ ዮሃንስ (የዘመን መለወጫ)በአል ከኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሺኝ ቀደም ብሎ ከቤተክርስትያናችን ጀርባ በሚገኘው ሥፍራ ላይ በአስደሳች ሁኔታ ሲከበር።




































ዘመን መለወጫ ከኮቪድ ወረርሺኝ በኋላ የደብራችን ሰንበት ተማሪዎች አበባየሆሽ በማለት በመዝሙር ሲያከብሩ።

የሕጻናትን ትምህርት በማጠናከር ረገድ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ተወያይቶ እንቅስቃሴው በዘመኑ ወረርሺኝ የመደናቀፍ እድል እንዳይገጥመው ሕጻናትን በእድሚያቸው እና በችሎታቸው በመከፋፈል ዘመኑ በፈቀደው የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ትምህርቱ እዲሰጥ ለማድረግ  የሕፃናት ትምህርት ክፍሉን የማበረታታት ተግባር ፈጽሞ ስኬትማ ሆኗል። 






ከኮቪድ ወረርሽኝ በፊት የሕጻናት ትምህርት እንቅስቃሴ ይህን ይመስል ነበር።






ከኮቪድ አስራ ዘጠኝ በፊት ሕፃናት በትንሣኤ እለት ምሽት በመዝሙር ሲያመሰግኑ።















ይህ ለእኛ ቤተክርስትያን ብቻ ሳይሆን ለመላው አለም አደገኛ እንቅፋት የሆነው የዘመኑን ወረርሺኝ ተቋቁሞ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት ሌላው ትልቁ የደብራችን ፈተና ቢሆንም ወረርሺኙ የደቀናቸውን እንቅፋቶች በመቋቋም በፈጣሪ እርዳታ መንፈሳዊ  አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ በደብራችን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ እና በደብራችን የካሕናት ጉባኤ የተደረገው ጥረት እጅግ ከፍተኛ እና ብልሃትን የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት የደብራችን ምእመናን እና ምእመናት ከወቅቱ ሁኔታ ጋር እራሳቸውን በማጣጠም ለጥረቱ መሳካት ያደረጉት ትብብር ከፍተኛ መሆኑ በዚህ አጋጣሚ መግለጽ ያሻል።ይህ ሰውን መግደል የሚችል ወረርሺኝ ተዛምቶ አለምን እና የምንኖርበትን አገር ባስጨነቀበት ወቅት የወረርሺኙን የመዛመት ፍጥነት መጨመርን እና መቀነስን መሰረት አድርገው የሚወጡ የመንግስት ሕግጋቶችን እና መመሪያዎችን በመከተል ለሁኔታው ተስማሚ የሆነ መርሃ ግብራትን በማዘጋጀት ምእመናን ቤተክርስትያናቸውን እና እምነታቸውን እንዳይዘነጉ ለማድረግ እየተደረገ ያለው እና የተደረገው ጥረት ከፍተኛ የአመራር ብስለት የሚጠይቅ ነበር።






ቅዱስ ጋብቻ ከኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሺኝ በፊት።














ቅዱስ ጋብቻ ከኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሺኝ በኋላ።

የወረርሺኙ ብዛት ሲበረታ ካሕናት እና ዲያቆናት ብቻ ወደ ቤተክርስትያን እንዲገቡ በማድረግ፣ወረርሺኙ የመስፋፋት  መጠኑ ሲቀንስ ምእመናን እና ምእመናትን ሕጉ በሚፈቅደው መጠን ወደ ቤተክርስትያን በማስገባት መንፈሳዊ አገልግሎቱ ሳይቋረጥ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ተችሏል።

እንደተለመደው ከሌላ ክፍለ አገር እና ከጎረቤት አገራት በሚመጡ ምእመናን እና ምእመናት የቅዱስ ገብርኤልን አመታዊ በአል ማክበር ባይቻልም ወረርሺኙን አስመልክቶ የወጣውን ሕግ ባልጣሰ እና ሕዝበ ክርስትያኑን ለወረርሺኙ በማያጋልጥ ሁኔታ በአሉን ለማክበር ተሞክሯል። የትንሳኤ በአል፣ የልደት በአል፣ጾመ ፍልሰታ እና ሌሎች ታላላቅ በአላትን አስመልክቶ የተዘጋጁ የጸሎት እና የቅዳሴ መርሃ ግብራትን ምእመናን እና ምእመናትን በቁጥር መጥኖ በማስገባት፣ የቀረው ሕዝበ ክርስትያን መርሃ ግብራቱን በየመኖርያ ቤቱ ሆኖ እንዲከታተል የቀጥታ ስርጭት በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በማስተላለፍ የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆን ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል።











የደብራችን ሚዲያ ክፍል አባል የቀጥታ ስርጭት በማስተላለፍ ላይ ሣለ።

በተለይ የጾመ ፍልሰታን መርሃ ግብራት እለቱን አራት ቦታ በመክፈል ከሌሊቱ አስር ሰአት እስከ ጠዋቱ ሁለት ሰአት መልክአ ስእል ተአምረ ማርያም ኪዳን የመሳሰሉትን፣ከቀኑ አራት ሰአት እስከ ስድስት ሰአት የውዳሴ ማርያም ትርጉም በደብራችን አስተዳዳሪ በሊቀ ብርሃናት አባ ያሬድ ምስጋናው፣ከስድስት ሰአት እስከ ዘጠኝ ሰአት ቅዳሴ፣ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰአት እስከ ምሽቱ ሁለት ሰአት ድረስ የሰርክ ጸሎት እና ስብከተ ወንጌል እንደ አንድ ትልቅ ገዳም በመስጠት የደብራችን ምእመናን እና ምእመናት  በሙሉ በተራ እየገቡ የአስራ ስድስቱንም ቀናት መርሃ ግብራት በመሳተፍ  የበረከቱ ተሳታፊ መሆን ችለዋል።

በዚሕ አጋጣሚ በአጭር ግዜ ውስጥ በአዲስ መልክ ተዋቅሮ በወረርሺኙ ምክንያት ቤተክርስትያን ተገኝተው የጸሎት እና የቅዳሴ መርሃ ግብር መሳተፍ ላልቻሉ  ምእመናን እና ምእመናት የቀጥታ ስርጭቱ በጥሩ ሁኔታ እንዲተላለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረገው የደብራችን የሚዲያ ክፍል ምስጋና ማቅረቡ እጅግ አስፈላጊ ነው።የሚዲያ ክፍሉ ከመደራጀቱ በፊት በእራሳቸው ተነሳሽነት የነበረውን የቀጥታ ስርጭት በስካይፒ በማስተላለፍ ይራዱ የነበሩ ወንድሞቻችንም በዚህ አጋጣሚ ማመስገን ይገባል።



 





















የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በአል ከኮቪድ ወረርሺኝ  በፊት።

















የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በአል ዋዜማ ከኮቪድ ወረርሺኝ በኋላ።


















የቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በአል ከኮቪድ በኋላ ይህን ይመስል ነበር።

የኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሺኝ ወደ አውሮፓ ተዛምቶ ጣልያን እና ስፔይንን ክፉኛ ባጠቃበት ወቅት ተመሳሳይ እልቂት እና ስቃይ እንዳይከሰት የጀርመን መንግስት ማንኛውንም እንቅስቃሴ ማድረግ ባገደበት ወቅት የእኛም ቤተ ክርስትያን ምእመናን እና ምእመናት በተገኙበት መንፈሳዊ አገልግሎት የመስጠት  እድል ከተነፈጉት አንዷ ብትሆንም የደብራችን ካሕናት እና ዲያቆናት የወረርሺኙን አደገኝነት ከምንም ሳይቆጥሩ አስፈላጊውን መስዋእትነት በመክፈል ያሳዩት ትጋት በሰውም በፈጣሪ ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስገኝላቸው ነው። ከደብሩ አስተዳዳሪ በስተቀር ሁለቱም ካህናት ቀሲስ ያሬድ እና ቀሲስ አትክልት ከዲቁና ማእረግ ወደ ቅስና ማእረግ ያደጉበትን ደብር አቅማቸው በፈቀደ ቤተሰቦቻቸውን ከሚያስተዳድሩበት ሥራ በተጨማሪ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ወረርሺኙን ሳይፈሩ ቤተክርስትያናቸውን በማገልገል ወደ ፊት እንደ እነሱ የቅስና ማእረግ ለሚጠብቃቸው ዲያቆናት መልካም ምሳሌ ለመሆን ችለዋል።

የደብራችን ዲያቆናት ከሊቀ ዲያቆኑ ጀምሮ ያሳዩት ትጋት እና የከፈሉት መስዋእትነት በደብራችን ምእመናን እና ምእመናት ዘንድ ከፍተኛ ክብር አስገኝቶላቸዋል።በፈጣሪ ዘንድም የበለጠ ክብር እንደሚያስገኝላቸው ጥርጥር የለውም።





ቀሲስ አትክልት የቅስና ማእረግ ከብጱእ አቡነ ናትናኤል  በሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ሲቀበሉ።












በጀርመን አገር ተወልደው የዲቁና ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ከነበሩ ታዳጊ ወጣቶች መኃከል ታዳጊ ወጣት ዮሃንስ ኃይለ ማርያም ከብጹዕ ወቅዱስ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዲዮናስዮስ የጀርመን እና የአካባቢው አውሮፓ አገራት አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የዲቁና ማእረግ ሲቀበል።

ይህ የሰው ሕይወት የሚቀጥፍ ወረርሺኝ በቤተክርስትያናችን መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረው ተጽእኖ እንደ ዋዛ የሚታይ አልነበረም።

በተለይ ወረርሺኙ ወደ አውሮፓ ተዛምቶ የደቡብ አውሮፓ አገሮችን ክፉኛ ባጠቃበት ወቅት ስለ ወረርሺኙ የነበረውም እውቀት እጅግም አልነበረም።በዚህ ወቅት የጀርመን መንግስት የወረርሺኙን መዛመት ለመቆጣጠር የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በቤተክርስትያናችን ላይ የመጣውን ተጽእኖ ለመቋቋም በተለይ በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ጫንቃ ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት ወድቆ ነበር።ቤተክርስትያን ተዘግቷል ማለት ይቻላል!

ከካሕናት በቀር ማንም ወደ ቤተ ክርስትያን መግባት አይችልም።ምእመናን እና ምእመናት ወደ ቤተክርስትያን ካልመጡ በወር ወደ አራት ሺህ ዩሮ የቤት ኪራይ ወጪ ያለበት ደብር እንዴት ከምእመናን እና ከምእመናት በተለያየ መንገድ የሚገኘው ገቢ እንዲህ ሊቀንስ በሚችልበት ሁኔታ የገንዘብ ችግር ሳይኖርበት መቀጠል ይችላል የሚለው ጥያቄ አንዱ ትልቅ ዱብ እዳ ነበር።ምክንያቱም ቤተክርስትያን ለምን ያህል ግዜ እንደሚዘጋ የሚታወቅ ነገር አልነበረም።

ሌላው ትልቁ ስጋት ምእመናን እና ምእመናት ከቤተክርስትያን ከራቁ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ላይ ስንፍናን ሊያሳዩና በዝያው ሊቀሩ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ሲሆን በተለይ የዋና አስተዳዳርያችን ከፍተኛ ጭንቀትም ሆኖ ታይቶ ነበር።ይህ ወረርሺኝ ብዙ የስራ እቅዶችን ማዛባቱ ብቻ ሳይሆን አዲስ ገጠመኝ ስለሆነ አዲስ ያልተለመደ አስተዳደራዊ ስራዎችን ለመስራት ያስገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል።የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ደብራችን ቀድሞ በነበረበት ጥንካሬው እንዲቀጥል ያለውን ችግር ለመጋፈጥ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በፈጠረው መንገድ በሳምንት ሁለቴ እና ሦስቴ እስከ እኩለ ሌሊት በመሰብሰብ እና ወቅቱ የሚጠይቀውን ውሳኔዎች በማስተላለፍ ቤተክርስትያናችን አሁን ባለችበት ሁኔታ እንትቀጥል አድርጓል ቢባል ማጋነን አይሆንም።በዚህ ግዜ ነው እንግዲህ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አባላት የሆኑት የደብራችን አስተዳዳሪ እና ቀሲስ አትክልትና ሊቀ ዲያቆን ዘውገ  አስቸኳይ ስብሰባ ቅዳሜ ምሽት እስከ ሃያ ሦስት ሰአት እና ዜሮ ሰአት ድረስ ተሰብስበው በሚቀጥለው ቀን
ለመቀደስ ቤተ ክርስትያን የሚገኙት።







ከግራ ወደ ቀኝ ቀሲስ አትክልት እሸቴ መኃከል ያሉት የደብራችን ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናው እና ቀሲስ ያሬድ ተሾመ።

የደብራችን ዋና አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናው ለአገሩ እንግዳ ቢሆኑም ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ጋር እጅና ጓንት በመሆን ይህን ክፉ ግዜ በመጋፈጥ ያሳዩት ችሎታ የሚደነቅ ነው።የወረርሺኙን የመዛመት ፍጥነት መሰረት ያደረጉትን ተለዋዋጭ ሕግጋቶችን በመከታተል ተስማሚ  የሆኑ መመርያዎችን በመቅረጽ  መንፈሳዊ አገልግሎቱ እና በተጓዳኝ አስተዳደራዊ ስራዎች ሊሰሩ ችለዋል።ከወዳጆቻችን ጋር  ማለትም ከካቶሊክ እና ከኢቫንጀሊካል ቤተክርስትያን ጋር ያለን ግንኙነት በፍጹም ወዳጅነት ቀጥሏል።የምኖርበት የዳሃውን ዲስትሪክት የፖለቲካ የባሕል የእምነት ኮሚቴም እቤተ ክርስትያን ድረስ ጋብዞ በበርካታ ቤተክርስትያናችንን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ለማነጋገር ተችሏል።



















የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ የዳሃው ዲስትሪክ ባለ ሥልጣናትን ወደ ደብራችን ጋብዞ ባነጋገረበት ወቅት።

ከላይ እንደተገለጸው የኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሺኝ በአገረ ጀርመን ተዛምቶ ቤተክርስትያን ለሕዝበ ክርስትያኑ ክፍት ባልሆነችበት ወቅት ይሁን ምእመናን እና ምእመናት በቁጥር እየተወሰኑ በገቡበትም ወቅት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ ስጋት ከአባላት በልዩ ልዩ አገልግሎት የሚገኙ ገቢዎች ስለሚቀንሱ በደብራችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር አስቀድሞ መገንዘብ ነበር።ለስጋቱ መበርታት ምክንያት የሆነው ወረርሺኙን ለመከላከል መንግስት የእንቅስቃሴ ገደብ በማወጁ በርካታ መስርያ ቤቶች ተዘግተው እንዲቆዩ ስለተደረገ የደብራችን አባላት ገቢ በዚህ አጋጣሚ የሚቀንስበት አጋጣሚ ሊፈጠር  ስለሚችል ምእመናን እና ምእመናት ከዚህ ቀደም ለቤተ ክርስትያናቸው ያደርጉት የነበረው የአባልነት ክፍያ ማሽቆልቆሉ የማይቀር ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የተደረሰ ሲሆን በተለይ ከተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚገኙ ገቢዎች ጨርሰው ይቋረጣሉ የሚለው ፍራቻ በወቅቱ መፍትሄ አልባ ሆኖ እንዳይቀጥል የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው አስተዳደሩ የቀየሳቸው መንገዶች ስኬት አምጥተው ይመጣል ተብሎ የተፈራው የገቢ እጥረት ተወግዶ በባሌ ጎባ እና በአሩሲ በተለየ ስሙ ሻሽመኔ ተብሎ በሚጠራው ከተማ አሳዛኝ ጭፍጨፋ እና የንብረት መውደም ለደረሰባቸው ምእመናን እርዳታ በማሰባሰብ አንድ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ለተረጂ ወገኖቻችን ለማድረስ ተችሏል።














ከኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሺኝ አስቀድሞ በለገጣፎ እና በአካባቢው የመኖርያ ቤታቸው ፈርሶባቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደሩ የተወከሉ አባላት እቦታው ተገኝተው ከሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የተላከ ላቸውን እርዳታ ሲያከፋፍሉ።










ከኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሺኝ በኋላ በባሌ ጎባ ለተፈናቀሉ እና ንብረታቸው ለወደመባ ው ወገኖች በብጱእ አቡነ ዮሴፍ አማካኝነት ከሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ምእመናን እና ምእመናት የተላከው አራት መቶ ሃምሳ ስምንት ሺሕ ብር እርዳታ ሲደርስ።










ብፁእ አቡነ ናትናኤል ከሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ምእመናን እና ምእመናት በአር ሲ ለተፈናቀሉ እና ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች የተላከውን የስምንት መቶ ሰባ አምስት ሺሕ ብር የባንክ ቼክ ለብፁእ አብነ ሄኖክ ለአርሲ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሲያስረክቡ።

ይሕ ብቻ ሳይሆን በሚገርም ሁኔታ በዚህ ወቅት ከአስተዳደራዊ ስራ የተረፈን ሃምሳ ሺሕ ዩሮ ከላይ ተጠቅሷል ወደ ቤተክርስትያን ማሰርያው የባንክ አካውንት እንዲገባ ተደርጓል።ይሕ ሁሉ እንቅስቃሴ ያለ ሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ምእመናን እና ምእመናት ታዛዥነት ተግባራዊ ሊሆን ስለማይችል ቤተክርስትያኑን እጅግ ለሚወደው  ሕዝበ ክርስትያን በእግዚአብሔር ስም ከፍተኛ ምስጋና ማቅረብ ይገባል!ይህ አለምን ያስጨነቀ ወረርሺኝ ለቤተክርስትያናችን ከፍተኛ ፈተና ቢሆንም በእግዚአብሔር ፈቃድ ፈተናውን በማለፍ መንፈሳዊ አገልግሎቱን እንደ 
ከዚህ በፊቱ ማከናወን ባይቻልም በተቻለ መጠን ሁሉም ነገር እንዳይቀር ሙከራ እየተደረገ ለዚህ ግዜ ደርሰናል።ወደ ፊትም በብጽኢት ድንግል ማርያም በወላዲት አምላክ አማላጅነት በመላኩ ቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት የቀረውን ፈተና አልፈን ወደ ቀደመው አገልግሎት እንደምንመለስ ጥርጥር የለንም!

















የታሕሣስ 29 2012ዓ.ም የልደት በአል ከኮቪድ ወረርሺኝ አስቀድሞ።







የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የሰበካ መ ንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አባላት።














የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስትያንን ከምስረታዋ ጀምሮ ያስተዳደሯት ፩ኛ/ ከቀኝ ወደ ግራ መልአከ ብርሃን ቀሲስ መስፍን ፈለቀ ከ1991-2011 ዓ.ም
ቆሞስ አባ ገብረ ሕይወት ፍሰሐ ( አቡነ ናትናኤል) ከ 2011-2018 ዓ.ም   ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናው ከ 2018 ዓ.ም ጀምሮ እያስተዳደሯት ይገኛሉ።

የሚዩኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ታሪክ ከሞላ ጎደል እንደ አውሮጳ አቆጣጠር  ከሺሕ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አንድ ዓ.ም ጀምሮ ያለው ይህን ይመስላል።አአነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልኡል እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን!

ይህን ታሪክ ለመጻፍ ስንነሳ የታሪኩ የመጀመርያው ክፍል የተሟላ እንዲሆን ግዚያቸውን ሰውተው በግምባር ከእኛ ጋር በመገናኘት እና አንዳንድ መረጃዎችን በማሥታወሻ መልክ አዘጋጅቶ በመስጠት የተባበሩንን እህቶቻችንን ወይዘሮ ሃናን እና ወይዘሮ መቅደስን ከልብ እናመሰግናለን!

ዶክተር ሄኖክ የታሪኩን የመጀመርያ ክፍል ተሟልቶ እንዲዘጋጅ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ሁለት የተለያዩ መጽሄቶችን በማቅረብ ላደረግህልን ትብብር ምስጋናችን የላቀ ነው!የቤተክርስትያናችን ታሪክ እንዲጻፍ የሃሳቡ ባለቤት የሆኑትን የደብራችን ዋና አስተዳዳሪን ቆሞስ አባ ያሬድ ምስጋናውንም በጣም እናመሰግናለን!

የሙንሽን ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የሚዲያ ክፍል።

አዘጋጅ ናደው መኮንን ተ/አረጋዊ።

Nadewu Mekonnen Teklearegawi 

2020 ዓ.ም